ምዕራፍ 30።

1፤ ለእስራኤልም አምላክ ለእግዚአብሔር ፋሲካ ያደርጉ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ቤት ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመጡ ሕዝቅያስ ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ላከ፥ ደግሞም ወደ ኤፍሬምና ወደ ምናሴ ደብዳቤ ጻፈ።

2፤3፤ ካህናቱም በሚበቃ ቍጥር ስላልተቀደሱ፥ ሕዝቡም ገና በኢየሩሳሌም ስላልተሰበሰቡ በጊዜው ያደርጉት ዘንድ አልቻሉምና ንጉሡና አለቆቹ የኢየሩሳሌምም ጉባኤ ሁሉ በሁለተኛው ወር ፋሲካውን ያደርጉ ዘንድ ተመካክረው ነበር።

4፤ ነገሩም ለንጉሡና ለጉባኤው ሁሉ ዓይን መልካም ነበረ።

5፤ እንደ ተጻፈም በብዙ ቍጥር አላደረጉም ነበርና የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ፋሲካ በኢየሩሳሌም ያደርጉ ዘንድ እንዲመጡ ከቤርሳቤህ ጀምሮ እስከ ዳን ድረስ ለእስራኤል ሁሉ አዋጅ እንዲነገር ወሰኑ።

6፤ እንደ ንጉሡም ትእዛዝ መልክተኞቹ እንዲህ የሚለውን የንጉሡንና የአለቆቹን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ። የእስራኤል ልጆች ሆይ፥ እግዚአብሔር ከአሦር ነገሥታት እጅ ወዳመለጠ ቅሬታችሁ እንዲመለስ ወደ አብርሃምና ወደ ይስሐቅ ወደ እስራኤልም አምላክ ተመለሱ።

7፤ እናንተም እንደምታዩ የተፈቱ እስኪያደርጋቸው ድረስ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን እንደ በደሉ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ።

8፤ አባቶቻችሁም እንደ ነበሩ አንገተ ደንዳና አትሁኑ፤ እጃችሁንም ለእግዚአብሔር ስጡ፥ ለዘላለም ወደ ተቀደሰው ወደ መቅደሱም ግቡ፥ ጽኑ ቍጣውም ከእናንተ እንዲመለስ አምላካችሁን እግዚአብሔርን አምልኩ።

9፤ አምላካችሁም እግዚአብሔር ቸርና መሐሪ ነውና፥ ወደ እርሱም ብትመለሱ ፊቱን ከእናንተ አያዞርምና ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁ በማረኩአቸው ፊት ምሕረትን ያገኛሉ፥ ደግሞም ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ።

10፤ መልእክተኞቹም ከከተማ ወደ ከተማ በኤፍሬምና በምናሴ አገር እስከ ዛብሎን ሄዱ፤ እነዚያ ግን በንቀት ሳቁባቸው፥ አፌዙባቸውም።

11፤ ነገር ግን ከአሴርና ከምናሴ ከዛብሎንም አያሌ ሰዎች ሰውነታቸውን አዋረዱ፥ ወደ ኢየሩሳሌምም መጡ።

12፤ ደግሞም አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ፥ በእግዚአብሔርም ቃል የሆነውን የንጉሡንና የአለቆቹን ትእዛዝ ያደርጉ ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ በይሁዳ ላይ ሆነ።

13፤ በሁለተኛውም ወር የቂጣውን በዓል ያደርግ ዘንድ እጅግ ታላቅ ጉባኤ የሆነ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተከማቸ።

14፤ ተነሥተውም በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎችና ለጣዖታት የሚያጥኑበትን ዕቃ ሁሉ አስወገዱ፥ በቄድሮንም ወንዝ ጣሉት።

15፤ በሁለተኛውም ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አረዱ፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም አፈሩ፥ ተቀደሱም፥ ወደ እግዚአብሔርም ቤት የሚቃጠል መሥዋዕት አመጡ።

16፤ እንደ እግዚአብሔርም ሰው እንደ ሙሴ ሕግ በሥርዓታቸው ቆሙ፤ ካህናቱም ከሌዋውያን እጅ የተቀበሉትን ደም ይረጩ ነበር።

17፤ በጉባኤውም ያልተቀደሱ እጅግ ሰዎች ነበሩ፤ ስለዚህም ሌዋውያን ለእግዚአብሔር ይቀድሱአቸው ዘንድ ንጹሐን ላልሆኑት ሁሉ ፋሲካውን ያርዱላቸው ነበር።

18፤ እንደ ትእዛዙም ሳይሆን ከኤፍሬምና ከምናሴ ከይሳኮርና ከዛብሎንም ወገን እጅግ ሰዎች ሳይነጹ ፋሲካውን በሉ።

19፤ ሕዝቅያስም። ምንም እንደ መቅደሱ ማንጻት ባይነጻ የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ልቡን የሚያቀናውን ሁሉ ቸሩ እግዚአብሔር ይቅር ይበለው ብሎ ስለ እነርሱ ጸለየ።

20፤ እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፥ ሕዝቡንም ፈወሰ።

21፤ በኢየሩሳሌምም ተገኝተው የነበሩ የእስራኤል ልጆች የቂጣውን በዓል በታላቅ ደስታ ሰባት ቀን አደረጉ፤ ሌዋውያኑና ካህናቱም በዜማ ዕቃ ለእግዚአብሔር እየዘመሩ ዕለት ዕለት እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።

22፤ ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያንን ሁሉ ያጽናና ነበር። የደኅንነትንም መሥዋዕት እያቀረቡ፥ የአባቶቻቸውንም አምላክ እያመሰገኑ ሰባት ቀን በዓል አደረጉ።

23፤24፤ የይሁዳም ንጉሥ ሕዝቅያስ ስለ ቍርባን ሺህ ወይፈኖችና ሰባት ሺህ በጎች ለጉባኤው ሰጥቶ ነበርና፥ አለቆቹም ሺህ ወይፈኖችና አሥር ሺህ በጎች ለጉባኤው ሰጥተው ነበርና፥ ከካህናቱም እጅግ ብዙ ተቀድሰው ነበርና ጉባኤው ሁሉ እንደ ገና ሰባት ቀን በዓል ያደርጉ ዘንድ ተማከሩ፤ በደስታም እንደ ገና ሰባት ቀን በዓል አደረጉ።

25፤ የይሁዳም ጉባኤ ሁሉ፥ ካህናቱና ሌዋውያኑ፥ ከእስራኤልም የመጡ ጉባኤ ሁሉ፥ ከእስራኤልም አገር የመጡትና በይሁዳ የኖሩት እንግዶች ደስ አላቸው።

26፤ በኢየሩሳሌምም ታላቅ ደስታ ሆነ፤ ከእስራኤል ንጉሥ ከዳዊት ልጅ ከሰሎሞን ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ በዓል በኢየሩሳሌም አልተደረገም ነበር።

27፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም ተነሥተው ሕዝቡን ባረኩ፤ ድምፃቸውም ተሰማ፥ ጸሎታቸውም ወደ ቅዱስ መኖሪያው ወደ ሰማይ ዐረገ።