ምዕራፍ 18።

1፤ ለኢዮሣፍጥም ብዙ ብልጥግናና ክብር ነበረው፤ ለአክዓብም ጋብቻ ሆነ።

2፤ ከጥቂት ዓመት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችንና በሬዎችን አረደ፥ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ይሄድ ዘንድ አባበለው።

3፤ የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን? አለው። እርሱም እኔ እንደ አንተ ነኝ፥ ሕዝቤም እንደ ሕዝብህ ናቸው፤ በሰልፍም ከአንተ ጋር እንሆናለን ብሎ መለሰለት።

4፤ ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ። የእግዚአብሔርን ቃል አስቀድመህ ትጠይቅ ዘንድ እለምንሃለሁ አለው።

5፤ የእስራኤልም ንጉሥ ነቢያቱን አራት መቶ ሰዎች ሰብስቦ። ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር? አላቸው። እነርሱም። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ አሉት።

6፤ ኢዮሣፍጥ ግን። እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔርን ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን? አለ።

7፤ የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁል ጊዜ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይነግርልኝምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው አለው። ኢዮሳፍጥም። ንጉሥ እንዲህ አይበል አለው።

8፤ የእስራኤልም ንጉሥ አንድ ጃንደረባ ጠርቶ። የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው አለው።

9፤ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሳፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማሪያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር።

10፤ የክንዓና ልጅ ሰዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ሶሪያውያንን እስኪጠፉ ድረስ በእነዚህ ትወጋለህ አለ።

11፤ ነቢያትም ሁሉ። እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ሂድና ተከናወን እያሉ እንዲሁ ትንቢት ይናገሩ ነበር።

12፤ ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ። እነሆ፥ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካም ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ አለው።

13፤ ሚክያስም። ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ አለ።

14፤ ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ። ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ እንሂድን? ወይስ እንቅር? አለው። እርሱም። ውጣ፥ ተከናወን፤ በእጅህም አልፈው ይሰጣሉ አለ።

15፤ ንጉሡም። በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ? አለው።

16፤ እርሱም። እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም። ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ ብሎ ተናገረ።

17፤ የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን። ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝም አላልሁህምን? አለው።

18፤ ሚክያስም አለ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይም ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው ቆመው አየሁ።

19፤ እግዚአብሔርም። ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን የሚያታልል ማን ነው? አለ። አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ።

20፤ መንፈስም መጣ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ። እኔ አታልለዋለሁ አለ። እግዚአብሔርም። በምን? አለው።

21፤ እርሱም። ወጥቼ በነቢያቱ ሁሉ አፍ ሐሰተኛ መንፈስ እሆናለሁ አለ። እግዚአብሔርም። ታታልለዋለህ፤ ይቀናሃል፤ ውጣ፥ እንዲህም አድርግ አለ።

22፤ አሁንም፥ እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ አፍ ሐሰተኛ መንፈስን አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።

23፤ የክንዓናም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፥ ሚክያስንም በጥፊ መታውና። የእግዚአብሔር መንፈስ ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ? አለ።

24፤ ሚክያስም። እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ወደ እልፍኝህ ስትሄድ ታያለህ አለ።

25፤ የእስራኤልም ንጉሥ። ሚክያስን ውሰዱ፥ ወደ ከተማይቱም አለቃ ወደ አሞን፥ ወደ ንጉሡም ልጅ ወደ ኢዮአስ መልሳችሁ።

26፤ ንጉሡ እንዲህ ይላል። በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፥ የመከራም እንጀራ መግቡት፥ የመከራም ውኃ አጠጡት በሉ አለ።

27፤ ሚክያስም። በደህና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ የተናገረ አይደለም አለ። ደግሞም። እናንተ ሕዝብ ሁሉ፥ ስሙኝ አለ።

28፤ የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ።

29፤ የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን። ልብሴን ለውጬ ወደ ሰልፍ እገባለሁ፤ አንተ ግን ልብስህን ልበስ አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፥ ወደ ሰልፍም ገቡ።

30፤ የሶርያም ንጉሥ የሰረገሎቹን አለቆች። ከእስራኤል ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትጋጠሙ ብሎ አዝዞ ነበር።

31፤ የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ። የእስራኤል ንጉሥ ነው አሉ፥ ሊጋጠሙትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፥ እግዚአብሔርም ረዳው፥ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው።

32፤ የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ እርሱን ከማሳደድ ተመለሱ።

33፤ አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳምባውን ወጋው። ሰረጋለኛውንም። ተወግቻለሁና እጅህን ግታ ከሰልፍም ውስጥ አውጣኝ አለው።

34፤ በዚያም ቀን ሰልፍ በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶሪያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሰረገላው ላይ ራሱን ይደግፍ ነበር፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሞተ።