ምዕራፍ 8።

1፤ እንዲህም ሆነ፤ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤትና የራሱን ቤት የሠራበት ሀያ ዓመት በተፈጸመ ጊዜ፥

2፤ ኪራም ለሰሎሞን የሰጠውን ከተሞች ሰሎሞን ሠራቸው፥ የእስራኤልንም ልጆች አኖረባቸው።

3፤ ሰሎሞንም ወደ ሐማትሱባ ሄደ አሸነፋትም።

4፤ በምድረ በዳም ያለውን ተድሞርን፥ በሐማትም የሠራቸውን የዕቃ ቤቱን ከተሞች ሁሉ ሠራ።

5፤ ደግሞም ቅጥርና መዝጊያ መወርወሪያም የነበራቸውን የተመሸጉትን ከተሞች ላይኛውን ቤትሖሮን ታችኛውንም ቤትሖሮን ሠራ።

6፤ ባዕላትንም፥ ለሰሎሞንም የነበሩትን የዕቃ ቤት ከተሞች ሁሉ፥ የሰረገላውንም ከተሞች ሁሉ፥ የፈረሰኞችንም ከተሞች፥ በኢየሩሳሌምም በሊባኖስም በመንግሥቱም ምድር ሁሉ ሰሎሞን ይሠራ ዘንድ የወደደውን ሁሉ ሠራ።

7፤ ከኬጢያውያንም ከአሞራውያንም ከፌርዜያውያንም ከኤዊያውያንም ከኢያቡሳውያንም የቀሩትን ከእስራኤል ወገን ያልሆኑትን ሕዝብ ሁሉ፥

8፤ የእስራኤልም ልጆች ያላጠፉአቸውን፥ በኋላቸው በምድር ላይ የቀሩትን ልጆቻቸውን ሰሎሞን እስከ ዛሬ ድረስ ገባሮች አድርጎ መለመላቸው።

9፤ ሰሎሞንም ለሥራው ከእስራኤል ልጆች ማንንም ባሪያ አላደረገም፤ እነርሱ ግን ሰልፈኞች፥ የሹማምቶችም አለቆች፥ የሰረገሎችና የፈረሰኞች ባልደራሶች ነበሩ።

10፤ እነዚህም በሕዝቡ ላይ ሠልጥነው የነበሩ የንጉሡ የሰሎሞን ዓይነተኞች አለቆች ሁለት መቶ አምሳ ነበሩ።

11፤ ሰሎሞንም። የእግዚአብሔር ታቦት የገባበት ስፍራ ቅዱስ ነውና ሚስቴ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት ቤት አትቀመጥም ሲል የፈርዖንን ልጅ ከዳዊት ከተማ ወደ ሠራላት ቤት አወጣት።

12፤ በዚያን ጊዜም ሰሎሞን በወለሉ ፊት በሠራው በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ለእግዚአብሔር የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቀረበ።

13፤ ሙሴም እንዳዘዘ እንደ ሥርዓታቸው በየቀኑ ሁሉ፥ በየሰንበታቱም፥ በየመባቻዎቹም፥ በየተወሰኑትም በዓላት፥ በየዓመቱ ሦስት ጊዜ በየቂጣው በዓልና በየሰባቱ ሱባዔ በዓል በየዳሱም በዓል ቍርባን ያቀርቡ ነበር።

14፤ የእግዚአብሔርም ሰው ዳዊት እንዲህ አዝዞ ነበርና ካህናቱን እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ሥርዓት በየአገልግሎታቸው ሰሞን ከፈላቸው፤ ሌዋውያንም እንደ ሥርዓታቸው ያመሰግኑ ዘንድ፥ በካህናቱም ፊት ያገለግሉ ዘንድ በየሰሞናቸው ከፈላቸው፤ በረኞቹንም ደግሞ በየበሩ ሁሉ በየሰሞናቸው ከፈላቸው።

15፤ እነርሱም ንጉሡ ስለ ነገሩ ሁሉና ስለ መዝገቡ ካህናቱንና ሌዋውያኑን ያዘዘውን ነገር ሁሉ አልተላለፉም።

16፤ የእግዚአብሔርም ቤት መሠረት ከተጣለ ጀምሮ እስከ ተጨረሰ ድረስ የሰሎሞን ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ነበረ። የእግዚአብሔርም ቤት ተፈጸመ።

17፤ ሰሎሞንም የዚያን ጊዜ በኤዶምያስ ምድር በባሕር ዳር ወዳሉ ወደ ዔጽዮንጋብርና ወደ ኤሎት ሄደ።

18፤ ኪራምም መርከቦችንና የባሕርን ነገር የሚያውቁትን መርከበኞች በባሪያዎቹ እጅ ሰደደለት፤ እነርሱም ከሰሎሞን ባሪያዎች ጋር ወደ ኦፊር መጡ፥ ከዚያም አራት መቶ አምሳ መክሊት ወርቅ ወስደው ወደ ንጉሡ ወደ ሰሎሞን አመጡ።