ምዕራፍ 31።

1፤ ፍልስጥኤማውያንም ከእስራኤል ጋር ተዋጉ፤ የእስራኤልም ሰዎች ከፍልስጥኤማውያን ፊት ሸሹ፥ ተወግተውም በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወደቁ።

2፤ ፍልስጥኤማውያንም ሳኦልንና ልጆቹን በእግር በእግራቸው ተከትለው አባረሩአቸው፤ ፍልስጥኤማውያንም የሳኦልን ልጆች ዮናታንንና አሚናዳብን ሜልኪሳንም ገደሉ።

3፤ ሰልፍም በሳኦል ላይ ጠነከረ፥ ቀስተኞችም አገኙት፤ እርሱም ከቀስተኞቹ የተነሣ እጅግ ተጨነቀ።

4፤ ሳኦልም ጋሻ ጃግሬውን። እነዚህ ቈላፋን መጥተው እንዳይወጉኝና እንዳይሳለቁብኝ ሰይፍህን መዝዘህ ውጋኝ አለው። ጋሻ ጃግሬው ግን እጅግ ፈርቶ ነበርና እንቢ አለ። ሳኦልም ሰይፉን ወስዶ በላዩ ወደቀ።

5፤ ጋሻ ጃግሬውም ሳኦል እንደ ሞተ ባየ ጊዜ እርሱ ደግሞ በሰይፉ ላይ ወደቀ፥ ከእርሱም ጋር ሞተ።

6፤ በዚያም ቀን ሳኦል ሦስቱም ልጆቹ ጋሻ ጃግሬውም ሰዎቹም ሁሉ በአንድ ላይ ሞቱ።

7፤ በሸለቆውም ማዶና በዮርዳኖስ ማዶ የነበሩ እስራኤላውያን የእስራኤል ሰዎች እንደ ሸሹ፥ ሳኦልና ልጆቹም እንደ ሞቱ ባዩ ጊዜ ከተሞቹን ለቅቀው ሸሹ፤ ፍልስጥኤማውያንም መጥተው ተቀመጡባቸው።

8፤ በማግሥቱም ፍልስጥኤማውያን የሞቱትን ለመግፈፍ በመጡ ጊዜ ሳኦልና ሦስቱ ልጆቹ በጊልቦዓ ተራራ ላይ ወድቀው አገኙአቸው።

9፤ የሳኦልንም ራስ ቈረጠው የጦር ዕቃውን ገፍፈው ለጣዖታቱ መቅደስ ለሕዝቡም የምስራች ይሰጥ ዘንድ ወደ ፍልስጥኤማውያን አገር ሁሉ ሰደዱ።

10፤ የጦር ዕቃውንም በአስታሮት መቅደስ ውስጥ አኖሩት፤ ሬሳውንም በቤትሳን ቅጥር ላይ አንጠለጠሉት።

11፤ ፍልስጥኤማውያንም በሳኦል ላይ ያደረጉትን የኢያቢስ ገለዓድ ሰዎች በሰሙ ጊዜ፥

12፤ ጀግኖች ሰዎች ሁሉ ተነሥተው ሌሊቱን ሁሉ ሄዱ፥ የሳኦልንም ሬሳ የልጆቹንም ሬሳ ከቤትሳን ቅጥር ላይ አወረዱ፤ ወደ ኢያቢስም መጡ፥ በዚያም አቃጠሉት።

13፤ አጥንታቸውንም ወሰዱ በኢያቢስም ባለው በአጣጡ ዛፍ በታች ቀበሩት፥ ሰባት ቀንም ጾሙ።