ምዕራፍ 28።

1፤ እንዲህም ሆነ፤ በዚያ ወራት ከእስራኤል ጋር ይዋጉ ዘንድ ፍልስጥኤማውያን ጭፍሮቻቸውን ለሰልፍ ሰበሰቡ፤ አንኩስም ዳዊትን። አንተና ሰዎችህ ከእኔ ጋር ወደ ሰልፍ እንድትወጡ በእርግጥ እወቅ አለው።

2፤ ዳዊትም አንኩስን። አሁን ባሪያህ የሚያደርገውን ታያለህ አለው። አንኩስም ዳዊትን። እንግዲህ በዘመኑ ሁሉ ራሴን ጠባቂ አደርግሃለሁ አለው።

3፤ ሳሙኤል ግን ሞቶ ነበር፥ እስራኤልም ሁሉ አልቅሰውለት ነበር፥ በከተማውም በአርማቴም ቀብረውት ነበር። ሳኦልም መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር አጥፍቶ ነበር።

4፤ ፍልስጥኤማውያንም ተሰብስበው መጡ በሱነምም ሰፈሩ፤ ሳኦልም እስራኤልን ሁሉ ሰበሰበ፥ በጊልቦዓም ሰፈሩ።

5፤ ሳኦልም የፍልስጥኤማውያንን ጭፍራ ባየ ጊዜ ፈራ፥ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ።

6፤ ሳኦልም እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እግዚአብሔርም በሕልም ወይም በኡሪም ወይም በነቢያት አልመለሰለትም።

7፤ ሳኦልም ባሪያዎቹን። ወደ እርስዋ ሄጄ እጠይቅ ዘንድ መናፍስትን የምትጠራ ሴት ፈልጉልኝ አላቸው፤ ባሪያዎቹም። እነሆ፥ መናፍስትን የምትጠራ አንዲት ሴት በዓይንዶር አለች አሉት።

8፤ ሳኦልም መልኩን ለውጦ ሌላ ልብስም ለብሶ ሄደ፥ ሁለትም ሰዎች ከእርሱ ጋር ነበሩ፥ በሌሊትም ወደ ሴቲቱ መጡ። እርሱም። እባክሽ፥ በመናፍስት አምዋርቺልኝ፥ የምልሽንም አስነሽልኝ አላት።

9፤ ሴቲቱም። እነሆ፥ መናፍስት ጠሪዎችንና ጠንቋዮችን ከምድር እንዳጠፋ ሳኦል ያደረገውን ታውቃለህ፤ ስለ ምን እኔን ለማስገደል ወጥመድ ለነፍሴ ታደርጋለህ? አለችው።

10፤ ሳኦልም። ሕያው እግዚአብሔርን! በዚህ ነገር ቅጣት አያገኝሽም ብሎ በእግዚአብሔር ማለላት።

11፤ ሴቲቱም። ማንን ላስነሣልህ? አለች፤ እርሱም። ሳሙኤልን አስነሽልኝ አለ።

12፤ ሴቲቱም ሳሙኤልን ባየች ጊዜ በታላቅ ድምፅ ጮኸች፤ ሴቲቱም ሳኦልን። አንተ ሳኦል ስትሆን ለምን አታለልኸኝ? ብላ ተናገረችው።

13፤ ንጉሡም። አትፍሪ፤ ያየሽው ምንድር ነው? አላት። ሴቲቱም ሳኦልን። አማልክት ከምድር ሲወጡ አየሁ አለችው።

14፤ እርሱም። መልኩ ምን ዓይነት ነው? አላት። እርስዋም። ሽማግሌ ሰው ወጣ፤ መጐናጸፊያም ተጐናጽፎአል አለች። ሳኦልም ሳሙኤል እንደ ሆነ አወቀ፥ በፊቱም ተጐነበሰ፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣ።

15፤ ሳሙኤልም ሳኦልን። ለምን አወክኸኝ? ለምንስ አስነሣኸኝ? አለው። ሳኦልም መልሶ። ፍልስጥኤማውያን ይወጉኛልና እጅግ ተጨንቄአለሁ፥ እግዚአብሔርም ከእኔ ርቆአል፤ በነቢያት ወይም በሕልም አልመለሰልኝም፤ ስለዚህም የማደርገውን ታስታውቀኝ ዘንድ ጠራሁህ አለው።

16፤ ሳሙኤልም አለ። እግዚአብሔር ከራቀህ ጠላትም ከሆነህ ለምን ትጠይቀኛለህ?

17፤ እግዚአብሔርም በቃሌ እንደ ተናገረ አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም መንግሥትህን ከእጅህ ነጥቆ ለጎረቤትህ ለዳዊት ሰጥቶታል።

18፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልሰማህምና፥ በአማሌቅም ላይ ታላቅ የሆነ ቍጣውን አላደረግህምና ስለዚህ ዛሬ እግዚአብሔር ይህን ነገር አድርጎብሃል።

19፤ እግዚአብሔርም እስራኤልን ከአንተ ጋር በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል፤ ነገም አንተና ልጆችህ ከእኔ ጋር ትሆናላችሁ፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ጭፍራ ደግሞ በፍልስጥኤማውያን እጅ አሳልፎ ይሰጣል።

20፤ ሳኦልም በዚያን ጊዜ በቁመቱ ሙሉ በምድር ላይ ወደቀ፥ ከሳሙኤልም ቃል የተነሣ እጅግ ፈራ። በዚያም ቀን ሁሉ በዚያም ሌሊት ሁሉ እንጀራ አልበላምና ኃይል አልቀረለትም።

21፤ ሴቲቱም ወደ ሳኦል መጣች፥ እጅግም ደንግጦ እንደ ነበረ አይታ። እነሆ፥ እኔ ባሪያህ ቃልህን ሰማሁ፥ ነፍሴንም በእጄ ጣልሁ፥ የነገርኸኝንም ቃል ሰማሁ።

22፤ አሁን እንግዲህ አንተ ደግሞ የባሪያህን ቃል እንድትሰማ እለምንሃለሁ፥ በፊትህም ቍራሽ እንጀራ ላኑርልህ፤ በመንገድም ስትሄድ ትበረታ ዘንድ ብላ አለችው።

23፤ እርሱ ግን። አልበላም ብሎ እንቢ አለ፤ ነገር ግን ባሪያዎቹና ሴቲቱ አስገደዱት፥ ቃላቸውንም ሰማ፤ ከምድርም ተነሥቶ በአልጋ ላይ ተቀመጠ።

24፤ ለሴቲቱም ማለፊያ እንቦሳ ነበራት፤ ፈጥና አረደችው፤ ዱቄቱንም ወስዳ ለወሰችው፥ ቂጣም እንጀራ አድርጋ ጋገረችው።

25፤ በሳኦልና በባሪያዎቹም ፊት አቀረበችው፤ በልተውም ተነሡ፥ በዚያም ሌሊት ሄዱ።