ምዕራፍ 26።

1፤ በረኞችም እንደዚህ ተመደቡ፤ ከቆሬያውያን ከአሳፍ ልጆች የቆሬ ልጅ ሜሱላም።

2፤ ሜሱላም ልጆች ነበሩት፤ በኵሩ ዘካርያስ፥ ሁለተኛው ይዲኤል፥ ሦስተኛው ዮዛባት፥

3፤ አራተኛው የትኒኤል፥ አምስተኛው ኤላም፥ ስድስተኛው ይሆሐናን፥ ሰባተኛው ኤሊሆዔናይ።

4፤ እግዚአብሔርም ባርኮታልና ዖቤድኤዶም ልጆች ነበሩት፤ በኵሩ ሸማያ፥ ሁለተኛው ዮዛባት፥ ሦስተኛው ኢዮአስ፥ አራተኛው ሣካር፥ አምስተኛው ናትናኤል፥

5፤ ስድስተኛው ዓሚኤል፥ ሰባተኛው ይሳኮር፥ ስምንተኛው ፒላቲ።

6፤ ለልጁም ለሸማያ ደግሞ ልጆች ተወለዱለት፤ ጽኑዓንም ኃያላን ነበሩና በአባታቸው ቤት ሠለጠኑ።

7፤ ለሸማያ ልጆች ዖትኒ፥ ራፋኤል፥ ዖቤድ፥ ወንድሞቹም ኃያላን የነበሩ ኤልዛባድ፥ ኤልሁ፥ ሰማክያ።

8፤ እነዚህ ሁሉ የዖቤድኤዶም ልጆች ነበሩ፤ እነርሱም ልጆቻቸውም ወንድሞቻቸውም ለማገልገል ኃያላን የነበሩ የዖቤድኤዶም ልጆች ስድሳ ሁለት ነበሩ።

9፤ ለሜሱላም ኃያላን የነበሩ አሥራ ስምንት ልጆችና ወንድሞች ነበሩት።

10፤ ከሜራሪም ልጆች ለነበረው ለሖሳ ልጆች ነበሩት፤ አለቃውም ሽምሪ ነበረ፤ በኵር አልነበረም፥ አባቱ ግን አለቃ አደረገው፤

11፤ ሁለተኛውም ኬልቅያስ፥ ሦስተኛው ጥበልያ፥ አራተኛው ዘካርያስ ነበረ፤ የሖሳ ልጆችና ወንድሞች ሁሉ አሥራ ሦስት ነበሩ።

12፤ እንደ ወንድሞቻቸው ሆነው በእግዚአብሔር ቤት ያገለግሉ ዘንድ የበረኞች የአለቆች ሰሞነኞች እነዚህ ነበሩ።

13፤ በበሩም ሁሉ ያገለግሉ ዘንድ በየአባቶቻቸው ቤቶች ታናሹና ታላቁ ተካክለው ዕጣ ተጣጣሉ።

14፤ በምሥራቅም በኩል ዕጣ ለሰሌምያ ወደቀ። ለልጁም ብልህ መካር ለሆነው ለዘካርያስ ዕጣ ጣሉ፤ ዕጣውም በሰሜን በኩል ወጣ።

15፤ ለዖቤድኤዶም በደቡብ በኩል፥ ለልጆቹም ለዕቃ ቤቱ ዕጣ ወጣ።

16፤ ለሰፊንና ለሖሳ በምዕራብ በኩል፥ በዐቀበቱም መንገድ ባለው በሸሌኬት በር በኩል ጥበቃ ከጥበቃ ላይ ዕጣ ወጣ።

17፤ በምሥራቅ በኩል ስድስት ሌዋውያን ነበሩ፤ በሰሜን በኩል ለየዕለቱ አራት፥ በደቡብ በኩል ለየዕለቱ አራት፥ ለዕቃ ቤቱም ሁለት ሁለት ነበሩ።

18፤ በምዕራብ በኩል በፈርባር መንገድ ላይ አራት፥ በፈርባርም አጠገብ ሁለት ነበሩ።

19፤ ከቆሬና ከሜራሪ ልጆች የነበሩ የበረኞች ሰሞን ይህ ነበረ።

20፤ ከሌዋውያን አኪያ በእግዚአብሔር ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብትና በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ላይ ተሾሞ ነበር።

21፤ የለአዳን ልጆች፤ ለለአዳን የሆኑ የጌድሶናውያን ልጆች፥ ለጌድሶናዊ ለለአዳን የሆኑ የአባቶች ቤቶች አለቆች ይሒኤሊ፤

22፤ የይሒኤሊ ልጆች፤ በእግዚአሔር ቤት በሚሆኑ ቤተ መዛግብት ላይ የነበሩ ዜቶም፥ ወንድሙም ኢዩኤል።

23፤ ከእንበረማውያን፥ ከይስዓራውያን፥ ከኬብሮናውያን፥ ከዑዝኤላውያን፤

24፤ የሙሴ ልጅ የጌርሳም ልጅ ሱባኤል በቤተ መዛግብት ላይ ተሾሞ ነበር።

25፤ ወንድሞቹም፤ ከአልዓዛር ልጁ ረዓብያ፥ ልጁም የሻያ፥ ልጁም ኢዮራም፥ ልጁም ዝክሪ፥ ልጁም ሰሎሚት መጡ።

26፤ ይህ ሰሎሚትና ወንድሞቹ ንጉሡ ዳዊትና የአባቶች ቤቶች አለቆች፥ ሻለቆችና የመቶ አለቆች የሠራዊቱም አለቆች፥ በቀደሱት በንዋየ ቅድሳቱ ቤተ መዛግብት ሁሉ ላይ ተሾመው ነበር።

27፤ በሰልፍም ከተገኘው ምርኮ የእግዚአብሔርን ቤት ለማበጀት ቀደሱ።

28፤ ባለ ራእዩም ሳሙኤል፥ የቂስም ልጅ ሳኦል፥ የኔርም ልጅ አበኔር፥ የጽሩያም ልጅ ኢዮአብ የቀደሱት ንዋየ ቅድሳት ሁሉ ከሰሎሚትና ከወንድሞቹ እጅ በታች ነበረ።

29፤ ከይስዓራውያን ከናንያና ልጆቹ ሹማምትና ፈራጆች ይሆኑ ዘንድ በውጭው ሥራ በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር።

30፤ ከኬብሮናውያን ሐሸብያና ወንድሞቹ፥ ጽኑዓን የነበሩት ሺህ ሰባት መቶ ሰዎች፥ ለእግዚአብሔር ሥራ ሁሉ ለንጉሡም አገልግሎት በዮርዳኖስ ማዶ በምዕራብ በኩል ባለው በእስራኤል ላይ ተሾመው ነበር።

31፤ ከኬብሮናውያንም እንደ አባቶች ቤቶች ትውልዶች የኬብሮናውያን አለቃ ይርያ ነበረ። ዳዊት በነገሠ በአርባኛው ዓመት ይፈልጉአቸው ነበር፤ በእነርሱም መካከል በገለዓድ ኢያዜር ጽኑዓን ኃያላን ሰዎች ተገኙ፤

32፤ ወንድሞቹም ጽኑዓን የነበሩት የአባቶች ቤቶች አለቆች ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። ንጉሡም ዳዊት ለእግዚአብሔር ጉዳይ ሁሉና ለንጉሡ ጉዳይ በሮቤላውያንና በጋዳውያን በምናሴም ነገድ እኵሌታ ላይ ሹሞች አደረጋቸው።