ምዕራፍ 24።

1፤ የአሮንም ልጆች ሰሞን ይህ ነው። የአሮን ልጆች ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር ነበሩ።

2፤ ናዳብና አብዩድ ግን ልጆች ሳይወልዱ ከአባታቸው በፊት ሞቱ፤ አልዓዛርና ኢታምርም ካህናት ሆኑ።

3፤ ዳዊትም ከአልዓዛር ልጆች ከሳዶቅ ጋር፥ ከኢታምርም ልጆች ከአቢሜሌክ ጋር ሆኖ እንደ አገልግሎታቸው ሥርዓት ከፍሎ መደባቸው።

4፤ የአልዓዛርም ልጆች አለቆች ከኢታምርም ልጆች አለቆች በልጠው ተገኙ፤ እንዲህም ተመደቡ፤ ከአልዓዛር ልጆች እንደ አባቶቻቸው ቤቶች አሥራ ስድስት፥ ከኢታምርም ልጆች እንደ አባቶቻቸው ቤቶች ስምንት አለቆች ነበሩ።

5፤ ከአልዓዛርና ከኢታምርም ልጆች መካከል የመቅደሱና የእግዚአብሔር አለቆች ነበሩና እነዚህና እነዚያ እንዲህ በዕጣ ተመደቡ።

6፤ ከሌዋውያንም ወገን የነበረው የናትናኤል ልጅ ጸሐፊው ሸማያ በንጉሡና በአለቆቹ ፊት፥ በካህኑ በሳዶቅና በአብያታርም ልጅ በአቢሜሌክ ፊት፥ በካህናቱና በሌዋውያኑ አባቶች ቤቶች አለቆች ፊት ጻፋቸው፤ አንዱንም የአባት ቤት ለአልዓዛር፥ አንዱንም ለኢታምር ጻፈ።

7፤ መጀመሪያውም ዕጣ ለዮአሪብ ወጣ፥ ሁለተኛው ለዮዳኤ፥

8፤ ሦስተኛው ለካሪም፥

9፤ አራተኛው ለሥዖሪም፥ አምስተኛው ለመልክያ፥

10፤ ስድስተኛው ለሚያሚን፥ ሰባተኛው ለአቆስ፥

11፤ ስምንተኛው ለአብያ፥ ዘጠኝኛው ለኢያሱ፥

12፤ አሥረኛው ለሴኬንያ፥ አሥራ አንደኛው ለኤልያሴብ፥ አሥራ ሁለተኛው ለያቂም፥

13፤ አሥራ ሦስተኛው ለኦፓ፥ አሥራ አራተኛው ለየሼብአብ፥

14፤ አሥራ አምስተኛው ለቢልጋ፥ አሥራ ስድስተኛው ለኢሜር፥

15፤ አሥራ ሰባተኛው ለኤዚር፥ አሥራ ስምንተኛው ለሃፊጼጽ፥

16፤ አሥራ ዘጠኝኛው ለፈታያ፥

17፤ ሀያኛው ለኤዜቄል፥ ሀያ አንደኛው ለያኪን፥ ሀያ ሁለተኛው ለጋሙል፥

18፤ ሀያ ሦስተኛው ለድላያ፥ ሀያ አራተኛው ለመዓዝያ።

19፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዳዘዘ፥ አባታቸው አሮን እንደ ሰጣቸው ሥርዓት ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚገቡበት የአገልግሎታቸው ሥርዓት ይህ ነበረ።

20፤ ከቀሩትም የሌዊ ልጆች፤ ከእንበረም ልጆች ሱባኤል፤ ከሱባኤል ልጆች ዬሕድያ፤

21፤22፤ ከረዓብያ ልጆች አለቃው ይሺያ፤ ከይስዓራውያን ሰሎሚት፤ ከሰሎሚት ልጆች ያሐት፤

23፤ ከኬብሮንም ልጆች አለቃው ይሪያ፥ ሁለተኛው አማርያ፥ ሦስተኛው የሕዚኤል፥ አራተኛው ይቀምዓም፤

24፤ የዑዝኤል ልጅ ሚካ፤

25፤ የሚካ ልጅ ሻሚር፤ የሚካ ወንድም ይሺያ፤

26፤ ከይሺያ ልጆች ዘካርያስ፤ የሜራሪ ልጆች ሞሖሊ፥ ሙሲ፤ ከያዝያ ልጅ በኖ፤

27፤ የሜራሪ ልጆች፤ ከያዝያ በኖ፥ ሾሃም፥ ዘኩር፥ ዔብሪ፤

28፤ ከሞሖሊ አልዓዛር፥ እርሱም ልጆች አልነበሩት፤

29፤ ከቂስ፤ የቂስ ልጅ ይረሕምኤል፤ የሙሲም ልጆች፤ ሞሖሊ፥ ዔዳር፥ ኢያሪሙት።

30፤ እነዚህ እንደ አባቶቻቸው ቤቶች የሌዋውያን ልጆች ነበሩ።

31፤ እነዚህም ደግሞ በንጉሡ በዳዊትና በሳዶቅ በአቢሜሌክም በሌዋውያንና በካህናት አባቶች ቤቶች አለቆች ፊት፥ ታላቁም እንደ ታናሹ፥ እንደ ወንድሞቻቸው እንደ አሮን ልጆች ዕጣ ተጣጣሉ።