ምዕራፍ 13።

1፤ በዚያ ቀን ለዳዊት ቤትና በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ከኃጢአትና ከርኵሰት የሚያነጻ ምንጭ ይከፈታል።

2፤ በዚያ ቀን፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፥ የጣዖታትን ስም ከምድር አጠፋለሁ፥ ከዚያም በኋላ አይታሰቡም፤ ደግሞም ሐሰተኞችን ነቢያትና ርኩስ መንፈስን ከምድር ላይ አስወግዳለሁ።

3፤ ማንም ደግሞ ትንቢት ቢናገር የወለዱት አባቱና እናቱ። አንተ በእግዚአብሔር ስም ሐሰትን ተናግረሃልና በሕይወት አትኖርም ይሉታል፤ ትንቢትንም ሲናገር የወለዱት አባቱና እናቱ ይወጉታል።

4፤ በዚያም ቀን ነቢያቱ ሁሉ ትንቢትን ሲናገሩ እያንዳንዱ ስለ ራእዩ ያፍራል፤ ያታልሉም ዘንድ የማቅ ልብስ አይለብሱም።

5፤ እርሱ ግን። ከታናሽነቴ ጀምሮ ባሪያ ሆኜ ነበርሁና ገበሬ ሰው ነኝ እንጂ ነቢይ አይደለሁም ይላል።

6፤ ሰውም። ይህ በእጅህ መካከል ያለ ቍስል ምንድር ነው? ይለዋል። እርሱም። በወዳጆቼ ቤት የቈሰልሁት ቍስል ነው ይላል።

7፤ ሰይፍ ሆይ፥ ባልንጀራዬ በሆነው ሰው በእረኛዬ ላይ ንቃ፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ እረኛውን ምታ፥ በጎቹም ይበተናሉ፤ እጄንም በታናናሾች ላይ እመልሳለሁ።

8፤ በምድርም ሁሉ ላይ ሁለት ክፍል ተቈርጠው ይሞታሉ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ሦስተኛውም ክፍል በእርስዋ ውስጥ ይቀራል።

9፤ ሦስተኛውንም ክፍል ወደ እሳት አገባለሁ፥ ብርም እንደሚነጥር አነጥራቸዋለሁ፥ ወርቅም እንደሚፈተን እፈትናቸዋለሁ፤ እነርሱም ስሜን ይጠራሉ፥ እኔም እሰማቸዋለሁ፤ እኔም። ይህ ሕዝቤ ነው እላለሁ፤ እርሱም። እግዚአብሔር አምላኬ ነው ይላል።