መዝሙር 82

የአሳፍ መዝሙር።

1 እግዚአብሔር በአማልክት ማኅበር ቆመ፥ በአማልክትም መካከል ይፈርዳል።

2 እስከ መቼ ሐሰትን ትፈርዳላችሁ? እስከ መቼ ለኃጢአተኞች ፊት ታደላላችሁ?

3 ለድሆችና ለድሀ አደጎች ፍረዱ፤ ለችግረኛውና ለምስኪኑ ጽድቅ አድርጉ፤

4 ብቸኛውንና ችግረኛውን አድኑ፤ ከኃጢአተኞችም እጅ አስጥሉአቸው።

5 አያውቁም፥ አያስተውሉም፤ በጨለማ ውስጥ ይመላለሳሉ፤ የምድር መሠረቶች ሁሉ ተናወጡ።

6 እኔ ግን። አማልክት ናችሁ፥ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ፤

7 ነገር ግን እንደ ሰው ትሞታላችሁ፥ ከአለቆችም እንደ አንዱ ትወድቃላችሁ አልሁ።

8 አቤቱ፥ ተነሥ፥ በምድር ላይ ፍርድ፥ አንተ አሕዛብን ሁሉ ትወርሳለህና።