መዝሙር 78

የአሳፍ ትምህርት።

1 ሕዝቤ ሆይ፥ ሕጌን አድምጡ፤ ጆሮአችሁንም ወደ አፌ ቃል አዘንብሉ።

2 አፌን በምሳሌ እከፍታለሁ፤ ከቀድሞ ጀምሮ፥ ያለውንም ተምሳሊት እናገራለሁ።

3 የሰማነውንና ያውቅነውን፥ አባቶቻችንም የነገሩንን፥ ለሚመጣ ትውልድ ከልጆቻቸው አልሰወሩም።

4 የእግዚአብሔርን ምስጋናና ኃይሉን ያደረገውንም ተኣምራት ተናገሩ።

5 ለልጆቻቸው ያስታውቅ ዘንድ ለአባቶቻችን ያዘዘውን ምስክር በያዕቆብ አቆመ፥ በእስራኤልም ሕግን ሠራ፤

6 የሚመጣ፥ ትውልድ የሚወለዱም ልጆች ያውቁ ዘንድ፥ ተነሥተው ለልጆቻቸው ይነግራሉ፤

7 ተስፋቸውን በእግዚአብሔር እንዲያደርጉ፥ የእግዚአብሔርንም ሥራ እንዳይረሱ፥ ትእዛዙንም እንዲጠብቁ፤

8 እንደ አባቶቻቸው እንዳይሆኑ ጠማማና የምታስመርር ትውልድ፥ ልብዋን ያላቀናች ትውልድ፥ ነፍስዋ በእግዚአብሔር ዘንድ ያልታመነች።

9 የኤፍሬም ልጆች ለሰልፍ ታጥቀው ቀስትንም ገትረው በሰልፍ ቀን ወደ ኋላ ተመለሱ።

10 የእግዚአብሔርን ኪዳን አልጠበቁም፥ በሕጉም ለመመላለስ እንቢ አሉ፤

11 መልካም ሥራውንና ያሳያቸውን ተኣምራቱን ረሱ፥

12 በግብጽ አገርና በጣኔዎስ በረሃ በአባቶቻቸው ፊት የሠራውን ተኣምራት።

13 ባሕርን ከፍሎ አሳለፋቸው፤ ውኆችን እንደ ክምር አቆመ።

14 ቀን በደመና መራቸው፥ ሌሊቱንም ሁሉ በእሳት ብርሃን።

15 ዓለቱን በምድረ በዳ ሰነጠቀ፤ ከጥልቅ እንደሚገኝ ያህል በብዙ አጠጣቸው።

16 ውኃን ከጭንጫ አወጣ፥ ውኃንም እንደ ወንዞች አፈሰሰ።

17 ነገር ግን ይበድሉት ዘንድ እንደ ገና ደገሙ፥ ልዑልንም በምድረ በዳ አስቈጡት።

18 ለነፍሳቸው መብልን ይፈልጉ ዘንድ፥ እግዚአብሔርን በልባቸው ፈተኑት።

19 እግዚአብሔርን እንዲህ ብለው አሙት። እግዚአብሔር በምድረ በዳ ማዕድን ያሰናዳ ዘንድ ይችላልን?

20 ዓለቱን መታ፤ ውኆችም ወጡ፥ ወንዞችም ጐረፉ፤ እንጀራን መስጠትስ ይችላልን? ለሕዝቡስ ማዕድን ያዘጋጃልን?

21 እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፤ በያዕቆብም ላይ እሳት ነደደ፥ መዓትም በእስራኤል ላይ መጣ፤

22 በእግዚአብሔር አላመኑምና፥ በመድኃኒቱም አልተማመኑምና።

23 ደመናውንም ከላይ አዘዘ፥ የሰማይንም ደጆች ከፈተ፤

24 ይበሉም ዘንድ መናን አዘነበላቸው፥ የሰማይንም እንጀራ ሰጣቸው።

25 የመላክትንም እንጀራ ሰው በላ ስንቅንም እስኪተርፋቸው ላከላቸው።

26 ከሰማይ የምሥራቅን ነፋስ አስነሣ፥ በኃይሉም የደቡብን ነፋስ አመጣ፤

27 ሥጋን እንደ አፈር፥ የሚበርሩትንም ወፎች እንደ ባሕር አሸዋ አዘነበላቸው፤

28 በሰፈራቸው መካከል፥ በድንኳናቸውም ዙሪያ ወደቀ።

29 በሉ እጅግም ጠገቡ፤ ምኞታቸውንም ሰጣቸው።

30 ከወደዱትም አላሳጣቸውም፤ መብላቸውም ገና በአፋቸው ሳለ፥

31 የእግዚአብሔር ቍጣ በላያቸው መጣ፥ ከእነርሱም ከፍ ያሉትን ገደለ፥ የእስራኤልንም ምርጦች አሰናከለ።

32 ከዚህም ሁሉ ጋር እንደ ገና በደሉ፥ ተኣምራቱንም አላመኑም፤

33 ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ፥ ዓመቶቻቸውም በችኰላ።

34 በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት፤ ተመለሱ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ፤

35 ረዳታቸውም እግዚአብሔር፥ መድኃኒታቸውም ልዑል አምላክ እንደ ሆነ አሰቡ።

36 በአፋቸው ብቻ ወደዱት፤ በአንደበታቸውም ዋሹበት፤

v37 ልባቸውም ከእርሱ ጋር አልቀናም፥ በቃል ኪዳኑም አልተማመኑትም።

38 እርሱ ግን መሓሪ ነው፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፤ ቍጣውንም መመለስ አበዛ፥ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም።

39 ወጥቶ የማይመለስ መንፈስ፥ ሥጋም እንደ ሆኑ አሰበ።

40 በምድረ በዳ ምን ያህል አስቈጡት፥ በበረሃም አሳዘኑት።

41 ተመለሱ፥ እግዚአብሔርንም ፈተኑት፥ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት።

42 እነርሱም እጁን አላሰቡም፥ ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀን፥

43 በግብጽ ያደረገውን ተኣምራቱን፥ በጣኔዎስም በረሃ ያደረገውን ድንቁን።

44 ወንዞቻቸውንም ወደ ደም ለወጠ፥ ምንጮቻቸውን ደግሞ እንዳይጠጡ።

45 ዝንቦችንም በላያቸው ሰደደባቸው፥ በሉአቸውም፤ በጓጉንቸርም አጠፋቸው።

46 ፍሬያቸውን ለኩብኩባ፥ ሥራቸውንም ለአንበጣ ሰጠ።

47 ወይናቸውን በበረዶ፥ በለሳቸውንም በአመዳይ አጠፋ።

48 እንስሶቻቸውን ለበረዶ፥ ሀብታቸውንም ለእሳት ሰጠ።

49 የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ፤ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ።

50 ለቍጣው መንገድን ጠረገ፤ ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም፥ እንስሶቻቸውንም በሞት ውስጥ ዘጋ፤

51 በኵሮቻቸውን ሁሉ በግብጽ፥ የድካማቸውንም መጀመሪያ በካም ድንኳኖች ገደለ።

52 ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው፥ እንደ መንጋም በምድረ በዳ መራቸው።

53 በተስፋም መራቸው አልፈሩምም፥ ጠላቶቻቸውንም ባሕር ደፈናቸው።

54 ወደ መቅደሱም ተራራ አገባቸው፥ ቀኙ ወደ ፈጠረችው ወደዚህች ተራራ፤

55 ከፊታቸውም አሕዛብን አባረረ፥ ርስቱንም በገመድ አካፈላቸው፥ የእስራኤልንም ወገኖች በቤታቸው አኖረ።

56 ነገር ግን ልዑል እግዚአብሔርን ፈተኑት አስቈጡትም፥ ምስክሩንም አልጠበቁም፤

57 ተመለሱም እንደ አባቶቻቸውም ከዱ፤ እንደ ጠማማ ቀስትም ተገለበጡ፤

58 በኰረብታ መስገጃዎቻቸውም አስቈጡት፥ በተቀረጹ ምስሎቻቸውም አስቀኑት።

59 እግዚአብሔርም ይህን ሰምቶ ተቈጣ፥ እስራኤልንም እጅግ ናቀ፤

60 የሴሎምን ማደሪያ ተዋት በሰዎች መካከል ያደረገባትን ድንኳኑን፤

61 ኃይላቸውን ለምርኮ፥ ሽልማቱንም በጠላት እጅ ሰጠ።

62 ሕዝቡንም በጦር ውስጥ ዘጋቸው፥ ርስቱንም ቸል አላቸው።

63 ጕልማሶቻቸውን እሳት በላቸው፥ ቈነጃጅቶቻቸውም አላዘኑም፤

64 ካህናቶቻቸውም በሰይፍ ወደቁ፥ ባልቴቶቻቸውም አላለቀሱላቸውም።

65 እግዚአብሔርም ከእንቅልፍ እንደሚነቃ ተነሣ፥ የወይን ስካር እንደ ተወው እንደ ኃያልም ሰው፤

66 ጠላቶቹንም በኋላቸው መታ፤ የዘላለምን ኀሣር ሰጣቸው።

67 የዮሴፍንም ድንኳን ተዋት፥ የኤፍሬምንም ወገን አልመረጠውም፤

68 የይሁዳን ወገን ግን መረጠ፥ የወደደውን የጽዮንን ተራራ።

69 መቅደሱን እንደ አርያም ሠራ፥ ለዘላለምም በምድር ውስጥ መሠረታት።

70 ዳዊትንም ባሪያውን መረጠው፥ ከበጎቹም መንጋ ውስጥ ወሰደው፤

71 ከሚያጠቡ በጎችም በኋላ፥ ባሪያውን ያዕቆብን ርስቱንም እስራኤልን ይጠብቅ ዘንድ ወሰደው።

72 በልቡ ቅንነት ጠበቃቸው፥ በእጁም ብልሃት መራቸው።