መዝሙር 75

ለመዘምራን አለቃ፤ አታጥፋ። የአሳፍ የምስጋና መዝሙር።

1 አቤቱ፥ እናመሰግንሃለን እናመሰግንሃለን ስምህንም እንጠራለን፤ ተኣምራትህን ሁሉ እናገራለሁ።

2 ጊዜውን ስቀበል እኔ በቅን እፈርዳለሁ።

3 ምድርና በእርስዋ ውስጥ የሚኖሩት ሁሉ ቀለጡ፥ እኔም ምሰሶችዋን አጠናሁ።

4 ዓመፀኞችን። አትበድሉ አልኋቸው፥ ኃጢአተኞችንም። ቀንዳችሁን አታንሡ፤

5 ቀንዳችሁን እስከ ላይ አታንሡ፥ በእግዚአብሔርም ላይ ዓመፅን አትናገሩ።

6 ክብር ከምሥራቅ ወይም ከምዕራብ ወይም ከምድረ በዳ የለምና፤

7 እግዚአብሔር ፈራጅ ነውና ይህን ያዋርዳል ይህንም ያከብራል።

8 ጽዋ በእግዚአብሔር እጅ ነውና፤ ያልተቀላቀለ የወይን ጠጅ ሞላበት፤ ከዚህ ወደዚያ አገላበጠው፥ ነገር ግን አተላው አልፈሰሰም፤ የምድር ኃጢአተኞች ሁሉ ይጠጡታል።

9 እኔ ግን ለዘላለም ደስ ይለኛል፥ ለያዕቆብም አምላክ ዝማሬን አቀርባለሁ።

10 የኅጥኣንን ቀንዶች ሁሉ እሰብራለሁ፤ የጻድቃን ቀንዶች ግን ከፍ ከፍ ይላሉ።