መዝሙር 74

የአሳፍ ትምህርት።

1 አቤቱ፥ ስለ ምን ለዘወትር ጣልኸኝ? በማሰማርያህ በጎች ላይስ ቍጣህን ስለ ምን ተቈጣህ?

2 አስቀድመህ የፈጠርሃትን ማኅበርህን፥ የተቤዤሃትንም የርስትህን በትር፥ በእርስዋ ያደርህባትን የጽዮንን ተራራ አስብ።

3 ጠላት በቅዱሳንህ ላይ እንደ ከፋ መጠን፥ ሁልጊዜም በትዕቢታቸው ላይ እጅህን አንሣ።

4 ጠላቶችህ በበዓል መካከል ተመኩ፤ የማያውቁትንም ምልክት ምልክታቸው አደረጉ።

5 እንደ ላይኛው መግቢያ ውስጥ በዱር እንዳሉም እንጨቶች፥ በመጥረቢያ በሮችዋን ሰበሩ።

6 እንዲሁ በመጥረቢያና በመዶሻ ሰበሩአት።

7 መቅደስህን በእሳት አቃጠሉ፤ የስምህንም ማደሪያ በምድር ውስጥ አረከሱ።

8 አንድ ሆነው በልባቸው በየሕዝባቸው። ኑ፥ የእግዚአብሔርን በዓሎች ከምድር እንሻር አሉ።

9 ምልክታችንን አናይም ከእንግዲህ ወዲህም ነቢይ የለም፤ እስከ መቼ እንዲኖር የሚያውቅ በኛ ዘንድ የለም።

10 አቤቱ፥ ጠላት እስከ መቼ ይሳደባል? ስምህን ጠላት ሁልጊዜ ያቃልላልን?

11 ቀኝህንም በብብትህ መካከል፥ እጅህንም ፈጽመህ ለምን ትመልሳለህ?

12 እግዚአብሔር ግን ከዓለም አስቀድሞ ንጉሥ ነው፥ በምድርም መካከል መድኃኒትን አደረገ።

13 አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት፤ አንተ የእባቦችን ራስ በውኃ ውስጥ ሰበርህ።

14 አንተም የዘንዶውን ራሶች ቀጠቀጥህ፤ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው።

15 አንተ ምንጮቹንና ፈሳሾቹን ሰነጠቅህ፤ አንተ ሁልጊዜ የሚፈስሱትን ወንዞች አደረቅህ።

16 ቀኑ የአንተ ነው ሌሊቱም የአንተ ነው፤ አንተ ፀሓዩንና ጨረቃውን አዘጋጀህ።

17 አንተ የምድርን ዳርቻ ሁሉ ሠራህ፤ በጋንም ክረምትንም አንተ አደረግህ።

18 ይህን ፍጥረትህን አስብ። ጠላት እግዚአብሔርን ተላገደ፥ ሰነፍ ሕዝብም ስሙን አስቈጣ።

19 የምትገዛልህን ነፍስ ለአራዊት አትስጣት፤ የችግረኞችህን ነፍስ ለዘወትር አትርሳ።

20 ወደ ኪዳንህ ተመልከት፥ የምድር የጨለማ ስፍራዎች በኅጥኣን ቤቶች ተሞልተዋልና።

21 ችግረኛ አፍሮ አይመለስ፤ ችግረኛና ምስኪን ስምህን ያመሰግናሉ።

22 አቤቱ፥ ተነሥ በቀልህንም ተበቀል፤ ሰነፎች ሁልጊዜም የተላገዱህን አስብ።

23 የባሪያዎችህን ቃል አትርሳ፤ የጠላቶችህ ኵራት ሁልጊዜ ወደ አንተ ይወጣል።