መዝሙር 70

ለመዘምራን አለቃ፤ ለመታሰቢያ፤ የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ እኔን ለማዳን ተመልከት፤ አቤቱ፥ እኔን ለመርዳት ፍጠን።

2 ነፍሴን የሚሹአት ይፈሩ ይጐስቍሉም፥ ክፉንም የሚመክሩብኝ ወደ ኋላቸው ይመለሱ ይፈሩም።

3 እንኳ እንኳ የሚሉኝ አፍረው ወዲያው ወደ ኋላቸው ይመለሱ።

4 የሚሹህ ሁሉ በአንተ ሐሤት ያድርጉ ደስ ይበላቸው፤ ማዳንህን የሚወድዱ ሁልጊዜ። እግዚአብሔር ታላቅ ነው ይበሉ።

5 እኔ ችግረኛና ምስኪን ነኝ፤ አቤቱ፥ እርዳኝ፤ ረዳቴ ታዳጊዬም አንተ ነህ፤ አቤቱ፥ አትዘግይ።