መዝሙር 56

ለመዘምራን አለቃ፤ ከቅዱሳን ስለ ራቁ ሕዝብ፤ ፍልስጥኤማውያን በጌት በያዙት ጊዜ፤ የዳዊት ቅኔ።

1 አቤቱ፥ ሰው ረግጦኛልና ማረኝ፤ ሁልጊዜም በሰልፍ አስጨንቆኛል።

2 የሚዋጉኝ በዝተዋልና ሁልጊዜ ቀኑን ሁሉ ጠላቶቼ ረገጡኝ።

3 እኔ ግን ፈራሁ በአንተም ታመንሁ።

4 በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፤ በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል?

5 ሁልጊዜ ቃሎቼን ያጸይፉብኛል፤ በእኔ ላይም የሚመክሩት ሁሉ ለክፉ ነው።

6 ይሸምቁብኛል ይሸሽጉኝማል፥ እነርሱም ተረከዜን ይመለካከታሉ፥ ሁልጊዜም ነፍሴን ይሸምቁባታል።

7 በምንም ምን አታድናቸውም፤ አሕዛብን በቍጣ ትጥላቸዋለህ።

8 አምላክ ሆይ፥ ሕይወቴን ነገርሁህ፤ እንባዬን እንደ ትእዛዝህ በፊተህ አኖርህ።

9 በጠራሁህ ጊዜ ጠላቶቼ ወደ ኋላቸው ይመለሳሉ፤ አንተ አምላኬ እንደ ሆንህ እነሆ፥ አወቅሁ።

10 በእግዚአብሔር ቃሉን አመሰግናለሁ፤ በእግዚአብሔር ቃሉን አከብራለሁ።

11 በእግዚአብሔር ታመንሁ፥ አልፈራም ሰው ምን ያደርገኛል?

12 አቤቱ፥ የምስጋና ስእለት የምሰጥህ ከእኔ ዘንድ ነው፤

13 ነፍሴን ከሞት፥ እግሮቼን ከመውደቅ አድነሃልና፥ በሕያዋን ብርሃን እግዚአብሔርን ደስ አሰኘው ዘንድ።