መዝሙር 28

የዳዊት መዝሙር።

1 አቤቱ፥ ወደ አንተ እጠራለሁ፤ ዝም ብትለኝ ወደ ጓድጓድ እንደሚወርዱት እንዳልመስል፥ አንተ አምላኬ፥ ዝም አትበለኝ።

2 ወደ መቅደስህ ማደሪያ እጄን ባነሣሁ ጊዜ፥ ወደ አንተ የጮኽሁትን የልመናዬን ቃል ስማ።

3 ከኃጥኣንና ከክፉ አድራጊዎች ጋር ነፍሴን አትውሰዳት፤ ክፋትም በልባቸው እያለ ከባልንጀራቸው ጋር ሰላም ከሚናገሩት ጋር አትጣለኝ።

4 እንደ ሥራቸው እንደ አካሄዳቸውም ክፉት ስጣቸው፤ እንደ እጃቸውም ሥራ ስጣቸው፤ ፍዳቸውን ወደ ራሳቸው መልስ።

5 ወደ እግዚአብሔር ሥራ ወደ እጆቹም አደራረግ አላሰቡምና ያፈርሳቸዋል እንጂ አይሠራቸውም።

6 የልመናዬን ቃል ሰምቶኛልና እግዚአብሔር ይመስገን።

7 እግዚአብሔር ኃይሌና ጋሻዬ ነው፤ ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ፤ ሥጋዬም ደስ ይለዋል፥ ፈቅጄም አመሰግነዋለሁ።

8 እግዚአብሔር ለሕዝቡ ኃይላቸው ነው፥ ለቀባውም የመድኃኒቱ መታመኛ ነው።

9 ሕዝብህን አድን፥ ርስትህንም ባርክ፤ ጠብቃቸው፥ ለዘላለሙም ከፍ ከፍ አድርጋቸው።