መዝሙር 107

ሃሌ ሉያ።

1 ቸር ነውና፥ ምሕረቱ ለዘላለም ነውና እግዚአብሔርን አመስግኑ፤

2 እግዚአብሔር ያዳናቸው፥ ከጠላቶች እጅ ያዳናቸው ይናገሩ።

3 ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከባሕር፥ ከየአገሩ ሰበሰባቸው።

4 ውኃ በሌለበት ምድረ በዳ ተቅበዘበዙ፤ የሚኖሩበትንም ከተማ መንገድ አላገኙም።

5 ተራቡ ተጠሙም፥ ነፍሳቸውም በውስጣቸው አለቀች።

6 በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው፤

7 ወደሚኖሩበት ከተማ ይሄዱ ዘንድ የቀና መንገድን መራቸው።

8 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤

9 የተራበችን ነፍስ አጥግቦአልና፥ የተራቈተችንም ነፍስ በበረከት ሞልቶአልና።

10 በጨለማ በሞትም ጥላ የተቀመጡ፥ በችግር በብረትም የታሰሩ፤

11 የእግዚአብሔርን ቃል ስለ ዐመፁ፥ የልዑልንም ምክር ስለ ናቁ፥

12 ልባቸው በድካም ተዋረደ፤ ታመሙ የሚረዳቸውም አጡ።

13 በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ በመከራቸውም አዳናቸው።

14 ከጨለማና ከሞት ጥላ አወጣቸው፥ እስራታቸውንም ሰበረ።

15 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ፤

16 የናሱን ደዶች ሰብሮአልና፥ የብረቱንም መወርወሪያ ቈርጦአልና።

17 ስለ ዓመፃቸው ሰነፉ፥ ስለ ኃጢአታቸውም ተቸገሩ።

18 ሰውነታቸው መብልን ሁሉ ተጸየፈች፥ ወደ ሞትም ደጆች ቀረቡ።

19 በተጨነቁ ጊዜም ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው።

20 ቃሉን ላከ ፈወሳቸውም፥ ከጥፋታቸውም አዳናቸው።

21 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተኣምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመሰግኑ፤

22 የምስጋና መሥዋዕትንም ይሠውለት፥ በእልልታም ሥራውን ይንገሩ።

23 በመርከቦች ወደ ባሕር የሚወርዱ፥ በታላቅ ውኃ ሥራቸውን የሚሠሩ፥

24 እነርሱ የእግዚአብሔርን ሥራ፥ በጥልቅም ያለችውን ድንቁን አዩ።

25 ተናገረ፥ ዐውሎ ነፋስም ተነሣ፥ ሞገድም ከፍ ከፍ አለ።

26 ወደ ሰማይ ይወጣሉ ወደ ጥልቅም ይወርዳሉ፤ ነፍሳቸውም በመከራ ቀለጠች።

27 ደነገጡ እንደ ስካርም ተንገደገዱ፥ ጥበባቸውም ሁሉ ተዋጠች።

28 በተጨነቁ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ፥ ከመከራቸውም አዳናቸው።

29 ዐውሎንም ጸጥ አደረገ፥ ሞገዱም ዝም አለ።

30 ዝም ብሎአልና ደስ አላቸው፤ ወደ ፈለጉትም ወደብ መራቸው።

31 ለሰው ልጆች ስላደረገው ተአምራት ስለ ምሕረቱም እግዚአብሔርን ያመስግኑ።

32 በአሕዛብ ጉባኤ ከፍ ከፍ ያድርጉት፥ በሽማግሌዎችም ሸንጎ ያመስግኑት።

33 ወንዞችን ምድረ በዳ፥ የውኃውንም ምንጮች ደረቅ አደረጋቸው፤

34 ከተቀመጡባት ክፋት የተነሣ ፍሬያማዋን ምድር ጨው አደረጋት።

35 ምድረ በዳን ለውኃ መቆሚያ፥ ደረቁንም ምድር የውኃ ምንጮች አደረገ።

36 በዚያም ራብተኞችን አስቀመጠ፥ የሚኖርባትንም ከተማ ሠሩ።

37 እርሻዎችንም ዘሩ ወይኖችንም ተከሉ፥ የእህልንም ሰብል አደረጉ።

38 ባረካቸውም እጅግም በዙ፤ እንስሶቻቸውንም አላሳነሰባቸውም።

39 እነርሱ በችግር በክፋት በጭንቀት ተዋረዱ እያነሱም ሄዱ፤

40 በአለቶችም ላይ ኅሣርን፥ አፈሰሰ፥ መንገድም በሌለበት በምድረ በዳ አሳታቸው።

41 ችግረኛንም ከችግሩ ረዳው፤ እንደ በጎች መንጋ ወገን አደረገው።

42 ቅኖች ያያሉ፥ ደስም ይላቸዋል፤ ኃጢአትም ሁሉ አፍዋን ትዘጋለች።

43 ጥበበኛ የሆነና ይህን የሚጠብቅ ማን ነው? እርሱ የእግዚአብሔርን ምሕረት ያስተውላል።