ምዕራፍ 27 (3)

1 ቀን የሚያመጣውን ምን እንደ ሆነ አታውቅምና ነገ በሚሆነው አትመካ።

2 ሌላ ያመስግንህ እንጂ አፍህ አይደለም፤ ባዕድ ሰው እንጂ ከንፈርህ አይደለም።

3 ድንጋይ ከባድ ነው አሸዋም ሸክሙ ጽኑ ነው፤ ከሁለቱ ግን የሰነፍ ቍጣ ይከብዳል።

4 ቍጣ ምሕረት የሌለው ነው፥ መዓትም እንደ ጎርፍ ነው፤ በቅንዓት ፊት ግን ማን ይቆማል?

5 የተገለጠ ዘለፋ ከተሰወረ ፍቅር ይሻላል።

6 የወዳጅ ማቍሰል የታመነ ነው፤ የጠላት መሳም ግን የበዛ ነው።

7 የጠገበች ነፍስ የማር ወላላ ትረግጣለች፤ ለተራበች ነፍስ ግን የመረረ ነገር ሁሉ ይጣፍጣታል።

8 ስፍራውን የሚተው ሰው፤ ቤቱን ትቶ እንደሚበርር ወፍ ነው።

9 ሽቱና ዕጣን ልብን ደስ ያሰኛሉ፤ እንዲሁ ነፍስ በወዳጁ ምክር ደስ ይላታል።

10 ወዳጅህንና የአባትህን ወዳጅ አትተው፤ በመከራህም ቀን ወደ ወንድምህ ቤት አትግባ፤ የቀረበ ወዳጅ ከራቀ ወንድም ይሻላል።

11 ልጄ ሆይ፥ ጠቢብ ሁን፥ ልቤንም ደስ አሰኘው፥ ለሚሰድበኝ መልስ መስጠት ይቻለኝ ዘንድ።

12 ብልህ ሰው ክፉን አይቶ ይሸሸጋል፤ አላዋቂዎች ግን አልፈው ይጐዳሉ።

13 ለማያውቀው ከተዋሰ ሰው ልብሱን ውሰድ፥ ለእንግዳ የተዋሰውንም እርሱን አግተው።

14 ባልንጀራውን በታላቅ ቃል ማለዳ የሚባርክ ሰው እንደሚራገም ያህል ነው።

15 በዝናብ ቀን የሚያንጠባጥብ ቤትና ጠበኛ ሴት አንድ ናቸው፤

16 እርስዋንም መከልከል ነፍስን መከልከልና ዘይትን በቀኝ እጅ መጨበጥ ነው።

17 ብረት ብረትን ይስለዋል፥ ሰውም ባልንጀራውን ይስላል።

18 በለሱን የጠበቀ ፍሬዋን ይበላል፥ ጌታውንም የሚጠብቅ ይከብራል።

19 ፊት በውኃ ላይ ለፊት እንደሚታይ፥ እንዲሁ የሰው ልብ ለሰው ይታያል።

20 ሲኦልና ጥፋት እንዳይጠግቡ፥ እንዲሁ የሰው ዓይን አይጠግብም።

21 ብር በከውር ወርቅም በማቅለጫ ይፈተናል፤ ሰውም በሚያመሰገኑት ሰዎች አፍ ይፈተናል።

22 ሰነፍን በሙቀጫ ውስጥ ከእህል ጋር በዘነዘና ብትወቅጠው፥ ስንፍናው ከእርሱ አይርቅም።

23 የበጎችህን መልክ አስተውለህ እወቅ፥ በከብቶችህም ላይ ልብህን አኑር፤

24 ባለጠግነት ለዘላለም አይኖርምና፥ ዘውድም ለትውልድ ሁሉ አይጸናምና።

25 ደረቅ ሣር በታጨደ ጊዜ፥ አዲስ ለምለም በታየ ጊዜ፥ ከተራራውም ቡቃያ በተሰበሰበ ጊዜ፥

26 በጎች ለልብስህ ፍየሎችም የእርሻ ዋጋ ይሆናሉ።

27 ለሲሳይህ ለቤተ ሰቦችህም ሲሳይ ለገረዶችህም ምግብ የፍየል ወተት ይበቃል።