ምዕራፍ 4

1 እናንተ ልጆች፥ የአባትን ተግሣጽ ስሙ፥ ማስተዋልንም ታውቁ ዘንድ አድምጡ፤

2 መልካም ትምህርትን እሰጣችኋለሁና፤ ሕጌን አትተዉ።

3 እኔም አባቴን የምሰማ ልጅ ነበርሁና፥ በእናቴም ዘንድ እወደድ ነበር።

4 ያስተምረኝም ነበር እንዲህም ይለኝ ነበር። ልብህ ቃሌን ይቀበል፤ ትእዛዜን ጠብቅ በሕይወትም ትኖራለህ።

5 ጥበብን አግኝ፤ ማስተዋልን አግኝ፤ አትርሳም፥ ከአፌም ቃል ፈቀቅ አትበል።

6 አትተዋት፥ ትደግፍህማለች፤ ውደዳት፥ ትጠብቅህማለች።

7 ጥበብ ዓይነተኛ ነገር ናትና ጥበብን አግኝ፤ ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ።

8 ከፍ ከፍ አድርጋት፥ እርስዋም ከፍ ከፍ ታደርግሃለች፤ ብታቅፋትም ታከብርሃለች።

9 ለራስህ የሞገስ አክሊልን ትሰጥሃለች፥ የተዋበ ዘውድንም ታበረክትሃለች።

10 ልጄ ሆይ፥ ስማ፥ ንግግሬንም ተቀበል፤ የሕይወትህም ዘመን ትበዛልሃለች።

11 የጥበብን መንገድ አስተማርሁህ፤ በቀናች ጎዳና መራሁህ።

12 በሄድህ ጊዜ እርምጃህ አይጠብብም፤ በሮጥህም ጊዜ አትሰናከልም።

13 ተግሣጽን ያዝ፥ አትተውም፤ ጠብቀው፥ እርሱ ሕይወትህ ነውና።

14 በኃጥኣን መንገድ አትግባ፥ በክፉ ሰዎችም ጎዳና አትሂድ።

15 ከእርስዋ ራቅ፥ አትሂድባትም፤ ፈቀቅ በል ተዋትም።

16 ክፉ ካላደረጉ አይተኙምና፥ ካላሰናከሉም እንቅልፋቸው ይወገዳልና።

17 የኃጢአትን እንጀራ ይበላሉና፥ የግፍንም ወይን ጠጅ ይጠጣሉና።

18 የጻድቃን መንገድ ግን እንደ ንጋት ብርሃን ነው፥ ሙሉ ቀን እስኪሆንም ድረስ እየተጨመረ ይበራል።

19 የኃጥኣን መንገድ እንደ ጨለማ ነው፥ እንዴት እንደሚሰናከሉም አያውቁም።

20 ልጄ ሆይ፥ ንግግሬን አድምጥ ወደ ቃሌም ጆሮህን አዘንብል።

21 ከዓይንህ አታርቃት፥ በልብህም ውስጥ ጠብቃት።

22 ለሚያገኙአት ሕይወት፥ ለሥጋቸውም ሁሉ ፈውስ ነውና።

23 አጥብቀህ ልብህን ጠብቅ፥ የሕይወት መውጫ ከእርሱ ነውና።

24 የአፍህን ጠማማነት ከአንተ አውጣ፥ ሐሰተኞቹን ከንፈሮችም ከአንተ አርቅ።

25 ዓይኖችህ አቅንተው ይዩ፥ ሽፋሽፍቶችህም በቀጥታ ይመልከቱ።

26 የእግርህን መንገድ አቅና፥ አካሄድህም ሁሉ ይጽና።

27 ወደ ቀኝም ወደ ግራም አትበል፤ እግርህንም ከክፉ መልስ።