ምዕራፍ 21።

1፤ በደቡብም በኩል ተቀምጦ የነበረው ከነዓናዊው የዓራድ ንጉሥ በአታሪም መንገድ እስራኤል እንደ መጡ ሰማ፤ ከእስራኤልም ጋር ሰልፍ አደረገ ከእነርሱም ምርኮ ማረከ።

2፤ እስራኤልም ለእግዚአብሔር። እነዚህን አሳልፈህ በእጄ ብትሰጣቸው ከተሞቻቸውን እርም ብዬ አጠፋለሁ ብሎ ስእለት ተሳለ።

3፤ እግዚአብሔርም የእስራኤልን ድምፅ ሰማ፥ ከነዓናውያንንም አሳልፎ ሰጣቸው፤ እነርሱንም ከተሞቻቸውንም እርም ብለው አጠፉ፤ የዚያንም ስፍራ ስም ሔርማ ብለው ጠሩት።

4፤ ከሖርም ተራራ ከኤዶምያስ ምድር ርቀው ሊዞሩ በኤርትራ ባሕር መንገድ ተጓዙ፤ የሕዝቡም ሰውነት ከመንገዱ የተነሣ ደከመ።

5፤ ሕዝቡም በእግዚአብሔርና በሙሴ ላይ። በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ ከግብፅ ለምን አወጣችሁን? እንጀራ የለም፥ ውኃ የለም፤ ሰውነታችንም ይህን ቀላል እንጀራ ተጸየፈ ብለው ተናገሩ።

6፤ እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ እባቦችን ሰደደ፥ ሕዝቡንም ነደፉ፤ ከእስራኤልም ብዙ ሰዎች ሞቱ።

7፤ ሕዝቡም ወደ ሙሴ መጥተው። በእግዚአብሔርና በአንተ ላይ ስለ ተናገርን በድለናል፤ እባቦችን ከእኛ ያርቅልን ዘንድ ወደ እግዚአብሔር ጸልይልን አሉት።

8፤ ሙሴም ስለ ሕዝቡ ጸለየ። እግዚአብሔርም ሙሴን። እባብን ሠርተህ በዓላማ ላይ ስቀል፤ የተነደፈውም ሁሉ ሲያያት በሕይወት ይኖራል አለው።

9፤ ሙሴም የናሱን እባብ ሠርቶ በዓላማ ላይ ሰቀለ፤ እባብም የነደፈችው ሰው ሁሉ የናሱን እባብ ባየ ጊዜ ዳነ።

10፤ የእስራኤልም ልጆች ተጓዙ፥ በኦቦትም ሰፈሩ።

11፤ ከኦቦትም ተጕዘው በሞዓብ ፊት ለፊት ባለችው ምድረ በዳ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል፥ በዒዬዓባሪም ሰፈሩ።

12፤ ከዚያም ተጕዘው በዘሬድ ሸለቆ ሰፈሩ።

13፤ ከዚያም ተጕዘው ከአሞራውያን ዳርቻ በሚወጣው ምድረ በዳ ውስጥ በአሮኖን ማዶ ሰፈሩ፤ አሮኖን በሞዓብና በአሞራውያን መካከል ያለ የሞዓብ ዳርቻ ነውና።

14፤ ስለዚህ በእግዚአብሔር የጦርነት መጽሐፍ እንዲህ ተባለ።

ዋሄብ በሱፋ፥

የአርኖንም ሸለቆች፥

15፤ ወደ ዔር ማደሪያ የሚወርድ

በሞዓብም ዳርቻ የሚጠጋ

የሸለቆች ፈሳሽ።

16፤ ከዚያም ወደ ብኤር ተጓዙ፤ ይኸውም እግዚአብሔር ሙሴን። ሕዝቡን ሰብስብ ውኃንም እሰጣቸዋለሁ ብሎ የተናገረለት ጕድጓድ ነው።

17፤ በዚያም ጊዜ እስራኤል ይህን መዝሙር ዘመረ።

አንተ ምንጭ ሆይ፥ ፍለቅ፤ እናንተ ዘምሩለት፤

18፤ በበትረ መንግሥት በበትራቸውም

የሕዝብ አዛውንቶች ያጐደጐዱት፥

አለቆችም የቈፈሩት ጕድጓድ።

19፤ ከምድረ በዳም ወደ መቴና ተጓዙ፤ ከመቴናም ወደ ነሃሊኤል፥ ከነሃሊኤልም ወደ ባሞት፥

20፤ ከባሞትም ምድረ በዳውን ከላይ ወደሚመለከተው ወደ ፈስጋ ተራራ ራስ በሞዓብ በረሀ ወዳለው ሸለቆ ተጓዙ።

21፤22፤ እስራኤልም። በምድርህ ላይ እንለፍ፤ ወደ እርሻና ወደ ወይን ቦታ አንገባም፤ ከጕድጓድም ውኃን አንጠጣም፤ ከምድርህ ዳርቻ እስክንወጣ ድረስ በንጉሥ ጐዳና እንሄዳለን ብለው ወደ አሞራውያን ንጉሥ ወደ ሴዎን መልእክተኞችን ላኩ።

23፤ ሴዎንም እስራኤል በምድሩ ላይ ያልፍ ዘንድ እንቢ አለ፤ ሴዎንም ሕዝቡን ሁሉ ሰበሰበ፥ እስራኤልንም ለመውጋት ወደ ምድረ በዳ ወጣ፥ ወደ ያሀጽም መጣ፥ ከእስራኤልም ጋር ተዋጋ።

24፤ እስራኤልም በሰይፍ መታው፥ ምድሩንም ከአርኖን ጀምሮ እስከ አሞን ልጆች እስከ ያቦቅ ድረስ ወረሰ፤ የአሞንም ልጆች ዳርቻ የጸና ነበረ።

25፤ እስራኤልም እነዚህን ከተሞች ሁሉ ወሰደ፤ እስራኤልም በአሞራውያን ከተሞች ሁሉ በሐሴቦንና በመንደሮቹ ሁሉ ተቀመጠ።

26፤ ሐሴቦንም የአሞራውያን ንጉሥ የሴዎን ከተማ ነበረ፤ እርሱም የፊተኛውን የሞዓብን ንጉሥ ወግቶ እስከ አርኖን ድረስ ምድሩን ሁሉ ከእጁ ወስዶ ነበር።

27፤ ስለዚህ በምሳሌ እንዲህ ተብሎ ተነገረ።

ወደ ሐሴቦን ኑ፤

የሴዎን ከተማ ይሠራ፥ ይመሥረት፤

28፤ እሳት ከሐሴቦን፥ ነበልባልም ከሴዎን ከተማ ወጣ፤

የሞዓብን ዔር፥ የአርኖንን ተራራ አለቆች በላ፤

29፤ ሞዓብ ሆይ፥ ወዮልህ!

የከሞስ ሕዝብ ሆይ፥ ጠፋህ፤

ወንዶች ልጆቹን ለሽሽት፥ ሴቶች ልጆቹንም ለምርኮ፥

ለአሞራውያን ንጉሥ ለሴዎን ሰጠ።

30፤ ገተርናቸው፤ ከሐሴቦን እስከ ዴቦን ድረስ ጠፉ፤

ኖፋም እስኪደርሱ እስከ ሜድባ አፈረስናቸው።

31፤ እስራኤልም እንደዚህ በአሞራውያን ምድር ተቀመጡ።

32፤ ሙሴም ሰላዮችን ወደ ኢያዜር ሰደደ፤ መንደሮችዋንም ወሰዱ፥ በዚያም የነበሩትን አሞራውያን አባረሩ።

33፤ ተመልሰውም በበሳን መንገድ ወጡ፤ የባሳንም ንጉሥ ዐግ ከሕዝቡ ሁሉ ጋር በኤድራይ ይወጋቸው ዘንድ ወጣ።

34፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። እርሱንና ሕዝቡን ሁሉ ምድሪቱንም አሳልፌ በእጅህ ሰጥቼአለሁና አትፍራው፤ በሐሴቦንም በተቀመጠው በአሞራውያን ንጉሥ በሴዎን እንዳደረግህ እንዲሁ ታደርግበታለህ አለው።

35፤ እርሱንና ልጆቹን ሕዝቡንም ሁሉ መቱ ሰውም አልቀረለትም፤ ምድሩንም ወረሱ።