ምዕራፍ 19።

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው።

2፤ እግዚአብሔር ያዘዘው የሕጉ ትእዛዝ ይህ ነው፤ መልካሚቱን፥ ነውርም የሌለባትን፥ ቀንበርም ያልተጫነባትን ቀይ ጊደር ያመጡልህ ዘንድ ለእስራኤል ልጆች ንገራቸው።

3፤ እርስዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ትሰጣላችሁ፥ እርስዋንም ከሰፈር ወደ ውጭ ይወስዳታል፥ አንድ ሰውም በፊቱ ያርዳታል።

4፤ ካህኑም አልዓዛር ከደምዋ በጣቱ ይወስዳል፥ ከደምዋም ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይረጫል።

5፤ ጊደሪቱም በፊቱ ትቃጠላለች፤ ቁርበትዋም ሥጋዋም ደምዋም ፈርስዋም ይቃጠላል።

6፤ ካህኑም የዝግባ እንጨት ሂሶጵም ቀይ ግምጃም ወስዶ ጊደሪቱ በምትቃጠልበት እሳት መካከል ይጥለዋል።

7፤ ካህኑም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ ከዚያም በኋላ ወደ ሰፈሩ ይገባል፤ ካህኑም እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል።

8፤ ያቃጠላትም ሰው ልብሱን በውኃ ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል።

9፤ ንጹሕም ሰው የጊደሪቱን አመድ ያከማቻል ከሰፈሩም ውጭ በንጹሕ ስፍራ ያኖረዋል፤ ርኵሰትም ለሚያነጻ ውኃ ለእስራኤል ልጆች ማኅበር ይጠበቃል፤ ከኃጢአት ለማንጻት የሚሆን ነው።

10፤ የጊደሪቱንም አመድ ያከማቸ ሰው ልብሱን ያጥባል እስከ ማታም ድረስ ርኩስ ይሆናል፤ ይህም ለእስራኤል ልጆች በመካከላቸውም ለሚኖር መጻተኛ ለዘላለም ሥርዓት ይሆናል።

11፤ የሞተውን ሰው በድን የሚነካ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል፤

12፤ በዚህም ውኃ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ያጠራል፥ ንጹሕም ይሆናል፤ ነገር ግን በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ሁለመናውን ባያጠራ ንጹሕ አይሆንም።

13፤ የሞተውን ሰው በድን የነካ ሁለመናውን ባያጠራ የእግዚአብሔርን ማደሪያ ያረክሳል፤ ያ ሰው ከእስራኤል ዘንድ ተለይቶ ይጠፋል፤ በእርሱም ላይ የሚያነጻ ውኃ አልተረጨምና ርኩስ ይሆናል፤ ርኵሰቱ ገና በእርሱ ላይ ነው።

14፤ ሰው በድንኳን ውስጥ ቢሞት ሕጉ ይህ ነው፤ ወደ ድንኳኑ የሚገባ ሁሉ በድንኳኑም ውስጥ ያለው ሁሉ ሰባት ቀን ርኵስ ይሆናል።

15፤ መክደኛው ያልታሰረ የተከፈተ ዕቃ ሁሉ ርኩስ ነው።

16፤ በሜዳም በሰይፍ የተገደለውን ወይም የሞተውን በድን ወይም የሰውን አጥንት ወይም መቃብር የሚነካ ሰባት ቀን ርኩስ ይሆናል።

17፤ ከኃጢአት ለማንጻት እንድትሆን ከተቃጠለችው ጊደር አመድ ለርኩሱ ይወስዱለታል፥ በዕቃውም ውስጥ የምንጭ ውኃ ይቀላቀልበታል።

18፤ ንጹሕም ሰው ሂሶጱን ወስዶ በውኃው ውስጥ ያጠልቀዋል፤ በድንኳኑም፥ በዕቃውም ሁሉ፥ በዚያም ባሉ ሰዎች ላይ፥ አጥንቱንም ወይም የተገደለውን ወይም የሞተውን ወይም መቃብሩን በነካው ላይ ይረጨዋል፤

19፤ ንጹሑም በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን በርኩሱ ላይ ይረጨዋል፤ ባሰባተኛውም ቀን ያጠራዋል፤ እርሱም ልብሱን ያጥባል፥ ገላውንም በውኃ ይታጠባል፥ በማታም ጊዜ ንጹሕ ይሆናል።

20፤ ሰውም ርኩስ ቢሆን ሁለመናውንም ባያጠራ፥ ያ ሰው የእግዚአብሔርን መቅደስ አርክሶአልና ከጉባኤው መካከል ተለይቶ ይጠፋል፤ በሚያነጻ ውኃ አልተረጨም፤ ርኩስ ነው።

21፤ ይህም የዘላለም ሥርዓት ይሆንላችኋል፤ የሚያነጻውን ውኃ የሚረጭ ሰው ልብሱን ያጥባል፤ የሚያነጻውንም ውኃ የሚነካ እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።

22፤ ርኩሱም የሚነካው ነገር ሁሉ ርኩስ ይሆናል፤ የሚነካውም ሰው እስከ ማታ ድረስ ርኩስ ይሆናል።