ምዕራፍ 13።

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

2፤ ለእስራኤል ልጆች የምሰጣትን የከንዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ሰዎችን ላክ፤ ከአባቶች ነገድ ሁሉ እያንዳንዱ በመካከላቸው አለቃ የሆነ አንድ ሰው ትልካላችሁ።

3፤ ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ትእዛዝ ከፋራን ምድረ በዳ ላካቸው፤ እነርሱም ሁሉ የእስራኤል ልጆች አለቆች ነበሩ።

4፤ ስማቸውም ይህ ነበረ፤ ከሮቤል ነገድ የዘኩር ልጅ ሰሙኤል፤

5፤ ከስምዖን ነገድ የሱሬ ልጅ ሰፈጥ፤

6፤ ከይሁዳ ነገድ የዮፎኒ ልጅ ካሌብ፤

7፤ ከይሳኮር ነገድ የዮሴፍ ልጅ ይግአል፤

8፤ ከኤፍሬም ነገድ የነዌ ልጅ አውሴ፤

9፤10፤ ከብንያም ነገድ የራፉ ልጅ ፈልጢ፤ ከዛብሎን ነገድ የሰዲ ልጅ ጉዲኤል፤

11፤ ከዮሴፍ ነገድ እርሱም የምናሴ ነገድ የሱሲ ልጅ ጋዲ፤

12፤ ከዳን ነገድ የገማሊ ልጅ ዓሚኤል፤

13፤ ከአሴር ነገድ የሚካኤል ልጅ ሰቱር፤

14፤ ከንፍታሌም ነገድ የያቢ ልጅ ናቢ፤

15፤ ከጋድ ነገድ የማኪ ልጅ ጉዲኤል።

16፤ ምድሪቱን ይሰልሉ ዘንድ ሙሴ የላካቸው ሰዎች ስም ይህ ነው። ሙሴም የነዌን ልጅ አውሴን ኢያሱ ብሎ ጠራው።

17፤ ሙሴም የከነዓንን ምድር ይሰልሉ ዘንድ ላካቸው፥ አላቸውም። ከዚህ በደቡብ በኩል ውጡ፥ ወደ ተራሮችም ሂዱ፤

18፤ ምድሪቱንም እንዴት እንደ ሆነች፥ በእርስዋም የሚኖሩ ሰዎች ብርቱዎች ወይም ደካሞች፥

19፤ ጥቂቶች ወይም ብዙዎች እንደ ሆኑ፥ የሚኖሩባትም ምድር መልካም ወይም ክፉ፥ የሚኖሩባቸውም ከተሞች ሰፈሮች ወይም አምቦች እንደ ሆኑ፥

20፤ ምድሪቱም ወፍራም ወይም ስስ ዛፍ ያለባት ወይም የሌለባት እንደ ሆነች እዩ፤ ከምድሪቱ ፍሬ አምጡ፤ አይዞአችሁ። በዚያን ጊዜም ወይኑ አስቀድሞ ፍሬ የሚያፈራበት ወራት ነበረ።

21፤ ወጡም ምድሪቱንም ከጺን ምድረ በዳ በሐማት ዳር እስካለችው እስከ ረአብ ድረስ ሰለሉ።

22፤ በደቡብም በኩል ውጡ፥ ወደ ኬብሮንም ደረሱ፤ በዚያም የዔናቅ ልጆች አኪመን፥ ሴሲ፥ ተላሚ ነበሩ። ኬብሮንም በግብፅ ካለችው ከጣኔዎስ በፊት ሰባት ዓመት ተሠርታ ነበር።

23፤ ወደ ኤሽኮልም ሸለቆ መጡ፥ ከዚያም ከወይኑ አንድ ዘለላ የነበረበትን አረግ ቈረጡ፥ ሁለቱም ሰዎች በመሎጊያ ተሸከሙት፤ ደግሞም ከሮማኑ ከበለሱም አመጡ።

24፤ የእስራኤል ልጆች ከዚያ ስለ ቈረጡት ዘለላ የዚያን ስፍራ ስም የኤሽኮል ሸለቆ ብለው ጠሩት።

25፤ ምድሪቱንም ሰልለው ከአርባ ቀን በኋላ ተመለሱ።

26፤ በፋራን ምድረ በዳና በቃዴስ ወዳሉት ወደ ሙሴና ወደ አሮን ወደ እስራኤልም ልጆች ማኅበር ሁሉ ሄደው ደረሱ፤ ወሬውንም ለእነርሱና ለማኅበሩ ሁሉ ነገሩአቸው፥ የምድሪቱንም ፍሬ አሳዩአቸው።

27፤ እንዲህም ብለው ነገሩት። ወደ ላክኸን ምድር ደረስን፥ እርስዋም ወተትና ማር ታፈስሳለች፥ ፍሬዋም ይህ ነው።

28፤ ነገር ግን በምድሪቱ የሚኖሩ ሰዎች ኃያላን ናቸው። ከተሞቻቸውም የተመሸጉ እጅግም የጸኑ ናቸው፤ ደግሞም በዚያ የዔናቅን ልጆች አየን።

29፤ በደቡብም ምድር አማሌቅ ተቀምጦአል፤ በተራሮቹም ኬጢያዊና ኢያቡሳዊ አሞራዊም ተቀምጠዋል፤ ከነዓናዊም በባሕር ዳርና በዮርዳኖስ አጠገብ ተቀምጦአል።

30፤ ካሌብም ሕዝቡን በሙሴ ፊት ዝም አሰኘና። ማሸነፍ እንችላለንንና እንውጣ፥ እንውረሰው አለ።

31፤ ከእርሱ ጋር የወጡ ሰዎች ግን። በኃይል ከእኛ ይበረታሉና በዚህ ሕዝብ ላይ መውጣት አንችልም አሉ።

32፤ ስለ ሰለሉአትም ምድር ክፉ ወሬ ለእስራኤል ልጆች እያወሩ። እኛ ዞረን የሰለልናት ምድር የሚኖሩባትን ሰዎች የምትበላ ምድር ናት፤ በእርስዋም ዘንድ ያየናቸው ሰዎች ሁሉ ረጃጅም ሰዎች ናቸው።

33፤ በዚያም ከኔፊሊም ወገን የሆኑትን ኔፊሊም፥ የዔናቅን ልጆች፥ አየን፤ እኛም በዓይናችን ግምት እንደ አንበጣዎች ነበርን፥ ደግሞም እኛ በዓይናቸው ዘንድ እንዲሁ ነበርን አሉ።