ምዕራፍ 3።

1፤ እግዚአብሔርም በሲና ተራራ ላይ ሙሴን በተናገረበት ቀን የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበረ።

2፤ የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው፤ በኵሩ ናዳብ፥ አብዩድ፥ አልዓዛር፥ ኢታምር።

3፤ የተቀቡ ካህናት በክህነትም ያገለግሉ ዘንድ የቀደሳቸው የአሮን ልጆች ስም ይህ ነው።

4፤ ናዳብና አብዩድ በሲና ምድረ በዳ በእግዚአብሔር ፊት ልዩ እሳት ባቀረቡ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ሞቱ፤ ልጆችም አልነበሩአቸውም። አልዓዛርና ኢታምር በአባታቸው በአሮን ፊት በክህነት ያገለግሉ ነበር።

5፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

6፤ የሌዊን ነገድ አቅርበህ ያገለግሉት ዘንድ በካህኑ በአሮን ፊት አቁማቸው።

7፤ የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ እርሱንና ማኅበሩን ሁሉ ለማገልገል የሚያስፈልገውን ነገር በመገናኛው ድንኳን ፊት ይጠብቁ።

8፤ የማደሪያውንም ሥራ ይሠሩ ዘንድ፥ የመገናኛውን ድንኳን ዕቃ ሁሉ ይጠብቁ፥ የእስራኤልን ልጆች ለማገልገል የሚያስፈልገውንም ነገር ይጠብቁ።

9፤ ሌዋውያንንም ለአሮንና ለልጆቹ ትሰጣለህ፤ ከእስራኤል ልጆች ለእርሱ ፈጽመው ተሰጡ።

10፤ አሮንንና ልጆቹን አቁማቸው፥ ክህነታቸውንም ይጠብቁ፤ ሌላ ሰውም ቢቀርብ ይገደል።

11፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

12፤ እነሆ፥ እኔ በእስራኤል ልጆች ዘንድ ማኅፀን በሚከፍተው በበኵሩ ሁሉ ፋንታ ሌዋውያንን ከእስራኤል ልጆች መካከል ወስጄአለሁ፤

13፤ በኵር ሁሉ ለእኔ ነውና ሌዋውያን ለእኔ ይሁኑ፤ በግብፅ ምድር በኵርን ሁሉ በመታሁ ቀን፥ ከእስራኤል ዘንድ በኵርን ሁሉ፥ ሰውንና እንስሳን፥ ለእኔ ለይቼአለሁ፤ ለእኔ ይሁኑ። እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

14፤ እግዚአብሔርም ሙሴን በሲና ምድረ በዳ እንዲህ ብሎ ተናገረው።

15፤ የሌዊን ልጆች በየአባቶቻቸው ቤቶች በየወገናቸውም ቍጠር፤ ወንዱን ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያለውን ቍጠራቸው።

16፤ ሙሴም እንደ እግዚአብሔር ቃል እንዳዘዘው ቈጠራቸው።

17፤ የሌዊ ልጆች በየስማቸው እነዚህ ናቸው፤ ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ።

18፤ የጌድሶንም ልጆች ስሞች በየወገናቸው እነዚህ ናቸው፤ ሎቤኒ፥ ሰሜኢ።

19፤ የቀዓትም ልጆች በየወገናቸው እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል።

20፤ የሜራሪም ልጆች በየወገናቸው፤ ሞሖሊ፥ ሙሲ። የሌዋውያን ወገኖች በየአባቶቻቸው ቤቶች እነዚህ ናቸው።

21፤ ለጌድሶን የሎቤናውያን ወገን የሰሜአውያንም ወገን ነበሩት፤ የጌድሶናውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው።

22፤ ከእነርሱ የተቈጠሩት የወንዶች ሁሉ ቍጥር ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ።

23፤ የጌድሶናውያን ወገኖች ከማደሪያው በኋላ በምዕራብ ብኩል ይሰፍራሉ።

24፤ የጌድሶናውያንም አባቶች ቤት አለቃ የዳኤል ልጅ ኤሊሳፍ ይሆናል።

25፤ ጌድሶናውያንም በመገናኛው ድንኳን የሚጠብቁት ማደሪያው፥ ድንኳኑም፥ መደረቢያውም፥ የመገናኛው ድንኳን ደጃፍ መጋረጃ፥

26፤ በማደሪያውና በመሠዊያው ዙሪያ ያለው የአደባባዩ መጋረጆች፥ የአደባባዩም ደጃፍ መጋረጃ፥ ለማገልገሉም ያሉት ገመዶች ሁሉ ይሆናል።

27፤ ከቀዓትም የእንበረማውያን ወገን፥ የይስዓራውያንም ወገን፥ የኬብሮናውያንም ወገን፥ የዑዝኤላውያንም ወገን ነበሩ፤ የቀዓታውያን ወገኖች እነዚህ ናቸው።

28፤ ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ፤ መቅደሱንም ይጠብቁ ነበር።

29፤ የቀዓት ልጆች ወገኖች በማደሪያው አጠገብ በደቡብ በኩል ይሰፍራሉ።

30፤ የቀዓታውያንም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የዑዝኤል ልጅ ኤሊሳፈን ይሆናል።

31፤ ታቦቱንም፥ ገበታውንም፥ መቅረዙንም፥ መሠዊያዎቹንም፥ የሚያገለግሉበትንም የመቅደሱን ዕቃ፥ መጋረጃውንም፥ ማገልገያውንም ሁሉ ይጠብቃሉ።

32፤ የሌዋውያንም አለቆች አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ይሆናል፤ እርሱም መቅደሱን በሚጠብቁት ላይ ይሆናል።

33፤ ከሜራሪ የሞሖላውያን ወገን የሙሳያውያንም ወገን ነበሩ፤ የሜራሪ ወገኖች እነዚህ ናቸው።

34፤ ከእነርሱም ወንዶች ሁሉ እንደ ቍጥራቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ የተቈጠሩት ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ።

35፤ የሜራሪም ወገኖች አባቶች ቤት አለቃ የአቢካኢል ልጅ ሱሪኤል ነበረ፤ በማደሪያው አጠገብ በሰሜን በኩል ይሰፍራሉ።

36፤ የሜራሪም ልጆች የሚጠብቁት የማደሪያው ሳንቆች፥ መወርወሪያዎችም፥ ተራዳዎችም፥ እግሮቹም፥ ዕቃውም ሁሉ፥

37፤ ማገልገያውም ሁሉ፥ በዙሪያውም የሚቆሙ የአደባባይ ምሰሶች፥ እግሮቹም፥ ካስማዎቹም፥ አውታሮቹም ይሆናሉ።

38፤ በማደሪያውም ፊት በምሥራቅ በኩል በመገናኛው ድንኳን ፊት በስተ ፀሐይ መውጫ የሚሰፍሩት ሙሴና አሮን ልጆቹም ይሆናሉ፥ መቅደሱንም ለእስራኤል ልጆች ይጠብቃሉ፤ ልዩም ሰው ቢቀርብ ይገደል።

39፤ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው፥ ከሌዋውያን ወንዶች ሁሉ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ በየወገናቸው የተቈጠሩት ሁሉ ሀያ ሁለት ሺህ ነበሩ።

40፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የእስራኤልን ልጆች ወንዱን በኵር ሁሉ ቍጠር፤ ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ያሉትን የስማቸውን ቍጥር ውሰድ፤

41፤ ሌዋውያንንም በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእስራኤል ልጆች እንስሶች በኵር ሁሉ ፋንታ ለእኔ ለእግዚአብሔር ውሰድ አለው።

42፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው የእስራኤልን ልጆች በኵር ሁሉ ቈጠረ።

43፤ ከእነርሱም የተቈጠሩ ወንዶች በኵሮች ሁሉ የበስማቸው ከአንድ ወር ጀምሮ ከዚያም በላይ ሀያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበሩ።

44፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

45፤ ሌዋውያንን በእስራኤል ልጆች በኵር ሁሉ ፋንታ፥ የሌዋውያንንም እንስሶች በእንስሶቻቸው ፋንታ ውሰድ፤ ሌዋውያንም ለእኔ ይሁኑ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

46፤ በሌዋውያን ላይ ከእስራኤል ልጆች በኵር ስለ ተረፉት ስለ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ቤዛ፥ በየራሱ አምስት ሰቅል ውሰድ፤

47፤ እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ትወስዳለህ፤ ሰቅሉም ሀያ አቦሊ ነው።

48፤ ስለ ተረፉትም የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።

49፤ ሙሴም በሌዋውያን ከተቤዡት በላይ ከተረፉት ዘንድ የመቤዣውን ገንዘብ ወሰደ።

50፤ ከእስራኤል ልጆች በኵሮች ገንዘቡን ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ አምስት ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ወሰደ።

51፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል፥ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው፥ ሙሴ የመቤዣውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ።