ምዕራፍ 4።

1፤ ሰንባላጥም ቅጥሩን እንደ ሠራን በሰማ ጊዜ እጅግ ተቈጣ፥ ተበሳጨም፥ በአይሁድም አላገጠ።

2፤ በወንድሞቹና በሰማርያ ሠራዊትም ፊት። እነዚህ ደካሞች አይሁድ የሚሠሩት ምንድር ነው? ይተዉላቸዋልን? ይሠዋሉን? በአንድ ቀንስ ይጨርሳሉን? የተቃጠለውንስ ድንጋይ ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን? ብሎ ተናገረ።

3፤ አሞናዊውም ጦብያ በአጠገቡ ቆሞ። በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል አለ።

4፤ አምላካችን ሆይ፥ ተንቀናልና ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው፤ በምርኮ አገር ለብዝበዛ አሳልፈህ ስጣቸው።

5፤ በደላቸውንም አትክደን፥ ኃጢአታቸውም ከፊትህ አይደምሰስ፤ በሠራተኞች ፊት አስቆጥተውሃልና።

6፤ ቅጥሩንም ሠራን፤ ቅጥሩም ሁሉ እስከ እኵሌታው ድረስ ተጋጠመ፤ የሕዝቡም ልብ ለሥራው ጨከነ።

7፤ ሰንባላጥና ጦብያም ዓረባውያንም አሞናውያንም አሽዶዳውያንም የኢየሩሳሌም ቅጥር እየታደሰ እንደ ሄደ፥ የፈረሰውም ሊጠገን እንደ ተጀመረ በሰሙ ጊዜ እጅግ ተቈጡ።

8፤ መጥተውም ኢየሩሳሌምን ይወጉና ያሸብሩ ዘንድ ሁሉም በአንድነት ተማማሉ።

9፤ ወደ አምላካችንም ጸለይን፥ ከእነርሱም የተነሣ በአንጻራቸው ተጠባባቂዎች በሌሊትና በቀን አደረግን።

10፤ ይሁዳም። የተሸካሚዎች ኃይል ደከመ፥ ፍርስራሹም ብዙ ነው፤ ቅጥሩንም እንሠራ ዘንድ አንችልም አሉ።

11፤ ጠላቶቻችንም። ወደ መካከላቸው እስክንመጣና እስክንገድላቸው ድረስ ሥራቸውንም እስክናስተጓጕል ድረስ አያውቁምና አያዩም አሉ።

12፤ በአጠገባቸውም የተቀመጡት አይሁድ መጥተው። ከስፍራው ሁሉ ይመጡብናል ብለው አሥር ጊዜ ነገሩን።

13፤ ከቅጥሩም በስተ ኋላ በኩል ባለው በታችኛው ስፍራ ሰይፋቸውን ጦራቸውንም ቀስታቸውንም አስይዤ ሕዝቡን በየወገናቸው አቆምኋቸው።

14፤ አይቼም ተነሣሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም የቀሩትንም ሕዝብ። አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፥ ስለ ወንድሞቻችሁም ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ አልኋቸው።

15፤ ጠላቶቻችንም ይህ ነገር እንደ ደረሰልን፥ እግዚአብሔርም ምክራቸውን ከንቱ እንዳደረገው ሰሙ፤ እኛም ሁላችን ወደ ቅጥሩ እያንዳንዳችን ወደ ሥራችን ተመለስን።

16፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ እኵሌቶቹ ብላቴኖቼ ሥራ ይሠሩ ነበር፥ እኵሌቶቹም ጋሻና ጦር ቀስትና ጥሩርም ይዘው ነበር፤ አለቆቹም ከይሁዳ ቤት ሁሉ በኋላ ይቆሙ ነበር።

17፤ ቅጥሩንም የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፥ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር።

18፤ አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር፤ ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ።

19፤ ታላላቆቹንና ሹማምቱን የቀሩትንም ሕዝብ። ሥራው ታላቅና ሰፊ ነው፥ እኛም በቅጥሩ ላይ ተበታትነናል፥ አንዱም ከሁለተኛው ርቆአል፤

20፤ የቀንደ መለከቱን ድምፅ ወደምትሰሙበት ስፍራ ወደዚያ ወደ እኛ ተሰብሰቡ፤ አምላካችን ስለ እኛ ይዋጋል አልኋቸው።

21፤ ሥራውንም ሠራን ከማለዳ ወገግታም ጀምሮ ከዋክብት እስኪወጡ ድረስ እኵሌቶቹ ጦር ይይዙ ነበር።

22፤ ደግሞም በዚያ ጊዜ ሕዝቡን። ሁላችሁ ከብላቴኖቻችሁ ጋር በኢየሩሳሌም ውስጥ እደሩ፤ በሌሊትም ጠባቂዎች ሁኑልን፥ በቀንም ሥሩ አልኋቸው።

23፤ እኔና ወንድሞቼም ብላቴኖቼም በኋላዬም የነበሩት ጠባቂዎች ልብሳችንን አናወልቅም ነበር።