ምዕራፍ 5።

1፤ የጭፍሮች ሴት ልጅ ሆይ፥ ጭፍሮችሽን አሁን ሰብስቢ፤ ከብቦ አስጨንቆናል፤ የእስራኤልን ፈራጅ ጕንጩን በበትር ይመታሉ።

2፤ አንቺም ቤተ ልሔም ኤፍራታ ሆይ፥ አንቺ በይሁዳ አእላፋት መካከል ትሆኚ ዘንድ ታናሽ ነሽ፤ ከአንቺ ግን አወጣጡ ከቀድሞ ጀምሮ ከዘላለም የሆነ፥ በእስራኤልም ላይ ገዥ የሚሆን ይወጣልኛል።

3፤ ስለዚህ ወላጂቱ እስከምትወልድበት ጊዜ ድረስ አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ የቀሩትም ወንድሞቹ ወደ እስራኤል ልጆች ይመለሳሉ።

4፤ እርሱም ይቆማል፥ በእግዚአብሔርም ኃይል በአምላኩ በእግዚአብሔር ስም ግርማ መንጋውን ይጠብቃል፤ እነርሱም ይኖራሉ፤ እርሱ አሁን እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ታላቅ ይሆናልና።

5፤ ይህም ለሰላም ይሆናል፤ አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፥ ምድራችንንም በረገጠ ጊዜ ሰባት እረኞችና ስምንት አለቆች እናስነሣበታለን።

6፤ የአሦርንም አገር በሰይፍ፥ የናምሩድንም አገር በመግቢያው ውስጥ ያፈርሳሉ፤ አሦራዊውም ወደ አገራችን በገባ ጊዜ፥ ዳርቾቻችንንም በረገጠ ጊዜ እርሱ ይታደገናል።

7፤ የያዕቆብም ቅሬታ በብዙ አሕዛብ መካከል ከእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚወርድ ጠል፥ በሣር ላይ እንደሚወድ ካፊያ፤ ሰውንም እንደማይጠብቅ፥ የሰውንም ልጆች ተስፋ እንደማያደርግ ይሆናል።

8፤ በዱር አራዊትም መካከል እንዳለ አንበሳ፥ በበጎች መንጋም መካከል አልፎ እንደሚረግጥ፥ የሚታደግም ሳይኖር እንደሚነጥቅ እንደ አንበሳ ደቦል፥ እንዲሁ የያዕቆብ ቅሬታ በአሕዛብና በብዙ ወገኖች መካከል ይሆናል።

9፤ እጅህ በጠላቶችህ ላይ ከፍ ከፍ ትበል፥ ጠላቶችህም ሁሉ ይጥፉ።

10፤ በዚያም ቀን ፈረሶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ሰረገሎችህንም እሰብራለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤

11፤ የምድርህንም ከተሞች አጠፋለሁ፥ ምሽጎችህንም ሁሉ አፈርሳለሁ፤

12፤ መተትንም ከእጅህ አጠፋለሁ፥ ምዋርተኞችም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆኑልህም፤

13፤ የተቀረጹትን ምስሎችህንና ሐውልቶችህን ከመካከልህ አጠፋለሁ፥ ለእጅህም ሥራ ከእንግዲህ ወዲህ አትሰግድም፤

14፤ የማምለኪያ ዐፀዶችህንም ከመካከልህ እነቅላለሁ፥ ከተሞችህንም አፈርሳለሁ።

15፤ ባልሰሙም አሕዛብ ላይ በቍጣና በመዓት እበቀላለሁ።