ምዕራፍ 24።

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

2፤ መብራቱን ሁልጊዜ እንድታበራበት ለመብራት ጥሩ ተወቅጦ የተጠለለ የወይራ ዘይት ያመጡልህ ዘንድ የእስራኤልን ልጆች እዘዛቸው።

3፤ በምስክሩ መጋረጃ ውጭ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ አሮን ከማታ እስከ ማለዳ ድረስ በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ ያሰናዳው፤ ለዘላለም ለልጅ ልጃችሁ ሥርዓት ይሁን።

4፤ በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ መቅረዝ ላይ መብራቶቹን ሁልጊዜ ያሰናዳቸው።

5፤ መልካሙንም ዱቄት ወስደህ አሥራ ሁለት ኅብስት ጋግር፤ በአንድ ኅብስት ውስጥ ከመስፈሪያው ከአሥር እጅ ሁለት እጅ ይሁን።

6፤ እነዚህንም ስድስት ስድስቱን በሁለት ተርታ አድርገህ በእግዚአብሔር ፊት በጥሩ ገበታ ላይ አኑራቸው።

7፤ ለእግዚአብሔርም ለእሳት ቍርባን በእንጀራው ላይ ለመታሰቢያ ይሆን ዘንድ በሁለቱ ተርታ ላይ ጥሩ ዕጣን አድርግ።

8፤ በእግዚአብሔር ፊት ሁልጊዜ በሰንበት ቀን ሁሉ በተርታ ያድርገው፤ በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ቃል ኪዳን ነው።

9፤ ለአሮንና ለልጆቹም ይሁን፤ በእሳት ከተደረገው ከእግዚአብሔር ቍርባን በዘላለም ሥርዓት ለእርሱ ቅዱስ ቅዱሳን ነውና በተቀደሰ ስፍራ ይብሉት።

10፤ አባቱ ግብፃዊ የነበረ የእስራኤላዊት ልጅ በእስራኤል ልጆች መካከል ወጣ፤ የእስራኤላዊቱ ልጅና አንድ እስራኤላዊ በሰፈር ውስጥ ተጣሉ፤

11፤ የእስራኤላዊቱም ልጅ የእግዚአብሔርን ስም ሰደበ፥ አቃለለውም፤ ወደ ሙሴም አመጡት። እናቱም ከዳን ነገድ የደብራይ ልጅ ነበረች፥ ስምዋም ሰሎሚት ነበረ።

12፤ ከእግዚአብሔርም አፍ ስለ እርሱ ፍርድ እስኪወጣላቸው ድረስ በግዞት አኖሩት።

13፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

14፤ ተሳዳቢውን ከስፈሩ ወደ ውጭ አውጣው፤ የሰሙትም ሁሉ እጃቸውን በራሱ ላይ ይጫኑበት፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገረው።

15፤ ለእስራኤልም ልጆች እንዲህ ብለህ ትነግራለህ። ማናቸውም ሰው አምላኩን ቢሰድብ ኃጢአቱን ይሸከማል።

16፤ የእግዚአብሔርንም ስም የሚሰድብ ፈጽሞ ይገደል፤ ማኅበሩም ሁሉ ይውገሩት፤ መጻተኛ ወይም የአገር ልጅ ቢሆን፥ የእግዚአብሔርን ስም በሰደበ ጊዜ ይገደል።

17፤ ሰውንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ፈጽሞ ይገደል።

18፤ እንስሳንም እስኪሞት ድረስ የሚመታ ሕይወት በሕይወት ፋንታ ካሣውን ይክፈል።

19፤ ሰውም ባልንጀራውን ቢጐዳ፥ እርሱ እንዳደረገ እንዲሁ ይደረግበት።

20፤ ስብራት በስብራት ፋንታ፥ ዓይን በዓይን ፋንታ፥ ጥርስ በጥርስ ፋንታ፥ ሰውን እንደ ጐዳ እንዲሁ ይደረግበት።

21፤ እንስሳውንም የሚገድል ካሣ ይተካ፤ ሰውንም የሚገድል ይገደል።

22፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝና ለመጻተኛና ለአገር ልጅ አንድ ዓይነት ሕግ ይሁንላችሁ።

23፤ ሙሴም ለእስራኤል ልጆች ተናገራቸው፤ ተሳዳቢውንም ከሰፈሩ ወደ ውጭ አወጡት፥ በድንጋይም ወገሩት። የእስራኤልም ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ።