ምዕራፍ 8።

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

2፤ አሮንን፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹን፥ ልብሱንም፥ የቅብዓቱንም ዘይት፥ ለኃጢአት መሥዋዕትም የሆነውን ወይፈን፥ ሁለቱንም አውራ በጎች፥ የቂጣውንም እንጀራ ሌማት ውሰድ፤

3፤ ማኅበሩንም ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሰብስባቸው።

4፤ ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ማኅበሩ ሁሉ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ ተሰበሰቡ።

5፤ ሙሴም ማኅበሩን። እግዚአብሔር ይደረግ ዘንድ ያዘዘው ነገር ይህ ነው አላቸው።

6፤ ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አቀረበ፥ በውኃም አጠባቸው።

7፤ ሸሚዝም አለበሰው፥ በመታጠቂያም አስታጠቀው፥ ቀሚስም አለበሰው፥ ኤፉድም ደረበለት፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቋድ አስታጠቀውና በእርሱ ላይ አሰረው።

8፤ የደረት ኪስ በእርሱ ላይ አደረገ፤ በደረቱ ኪስም ውስጥ ኡሪምንና ቱሚምን አኖረበት።

9፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው በራሱ ላይ መጠምጠሚያውን አደረገ፤ በመጠምጠሚያውም ላይ በፊቱ በኩል የተቀደሰውን አክሊል፥ ቅጠል የሚመስለውን የወርቅ ምልክት፥ አደረገ።

10፤ ሙሴም የቅብዓቱን ዘይት ወሰደ፥ ማደሪያውንና በውስጡ ያለውን ሁሉ ቀብቶ ቀደሳቸው።

11፤ ከእርሱም በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ረጨ፤ ይቀድሳቸውም ዘንድ መሠዊያውንና ዕቃውን ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውን ቀባ።

12፤ ከቅብዓቱም ዘይት በአሮን ራስ ላይ አፈሰሰ፥ ይቀድሰውም ዘንድ ቀባው።

13፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ሙሴ የአሮንን ልጆች አቀረበ፥ ቀሚሶችንም አለበሳቸው፥ በመታጠቂያም አስታጠቃቸው፥ ቆብም ደፋባቸው።

14፤ የኃጢአትንም መሥዋዕት ወይፈን አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በኃጢአቱ መሥዋዕት ወይፈን ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ።

15፤ አረደውም፤ ሙሴም ደሙን ወስዶ በጣቱ የመሠዊያውን ቀንዶች ዙሪያ ቀባ፥ መሠዊያውንም አነጻው፤ ደሙንም ከመሠዊያው በታች አፈሰሰው፥ ያስተሰርይለትም ዘንድ ቀደሰው።

16፤ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች ስባቸውንም ወሰደ፤ ሙሴም በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።

17፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዳዘዘው ወይፈኑን፥ ቁርበቱንም፥ ሥጋውንም፥ ፈርሱንም ከሰፈሩ ውጭ በእሳት አቃጠለ።

18፤ ለሚቃጠል መሥዋዕትም የሚሆን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ።

19፤ አረደውም፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨው።

20፤ አውራውንም በግ በየብልቱ ቈረጠ፤ ሙሴም ጭንቅላቱን ብልቶቹንም ስቡንም አቃጠለ።

21፤ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም በውኃ አጠበ፤ ሙሴም አውራውን በግ ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤ ይህ ጣፋጭ ሽታ እንዲሆን የሚቃጠል መሥዋዕት ነበረ፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነበረ።

22፤ ለቅድስናም የሚሆነውን ሁለተኛውን አውራ በግ አቀረበ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ጫኑ።

23፤ አረደውም፤ ሙሴን ከደሙ ወስዶ የአሮንን የቀኝ ጆሮውን ጫፍ፥ የቀኝ እጁንም አውራ ጣት የቀኝ እግሩንም አውራ ጣት አስነካው።

24፤ የአሮንንም ልጆች አቀረበ፤ ሙሴም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀን እጃቸውንም አውራ ጣት፥ የቀኝ እግራቸውንም አውራ ጣት ከደሙ አስነካ፤ ሙሴም ደሙን በመሠዊያው ዙሪያ ረጨ።

25፤ ስቡንና ላቱን፥ በሆድ ዕቃውም ላይ ያለውን ስብ ሁሉ፥ የጕበቱንም መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች ስባቸውንም፥ ቀኝ ወርቹንም ወሰደ፤

26፤ በእግዚአብሔር ፊት ካለው ከቂጣው እንጀራ ሌማት አንድ የቂጣ እንጐቻ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ ወስዶ በስቡና በቀኝ ወርቹ ላይ አኖራቸው።

27፤ ሁሉንም በአሮንና በልጆቹ እጆች ላይ አደረገ፥ በእግዚአብሔርም ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዛቸው።

28፤ ሙሴም ከእጃቸው ተቀብሎ በመሠዊያው በሚቃጠለው መሥዋዕት ላይ አቃጠለው፤ የጣፋጭ ሽታ መቀደሻ ነበረ። እርሱም ለእግዚአብሔር የእሳት ቁርባን ነበረ።

29፤ ሙሴም ፍርምባውን ወስዶ በእግዚአብሔር ፊት ለመወዝወዝ ቍርባን ወዘወዘው፤ እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው ይህ ለቅድስና ከታረደው አውራ በግ የሙሴ እድል ፈንታ ሆነ።

30፤ ሙሴም ከቅብዓቱ ዘይትና በመሠዊያው ላይ ካለው ከደሙ ወስዶ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ በልጆቹና በልጆቹ ልብስ ላይ ረጨው፤ አሮንንና ልብሱንም፥ ልጆቹንም የልጆቹንም ልብስ ቀደሰ።

31፤ ሙሴም አሮንንና ልጆቹን አላቸው። ሥጋውን በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ቀቅሉ፤ አሮንና ልጆቹ ይበሉታል ብዬ እንዳዘዝሁ በዚያ እርሱንና በሌማቱ ያለውን የቅድስናውን እንጀራ ብሉ።

32፤ ከሥጋውና ከእንጀራውም የተረፈውን በእሳት ታቃጥሉታላችሁ።

33፤ ሰባት ቀን ይክናችኋልና የክህነታችሁ ቀን እስኪፈጸም ድረስ ሰባት ቀን ከማኅበሩ ድንኳን ደጃፍ አትውጡ።

34፤ በዚህ ቀን እንደ ተደረገ ለእናንተ ለማስተስረያ ይደረግ ዘንድ እንዲሁ እግዚአብሔር አዘዘ።

35፤ እግዚአብሔር እንዲሁ አዝዞኛልና እንዳትሞቱ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ ሌሊቱንና ቀኑን ሰባት ቀን ተቀመጡ፥ የእግዚአብሔርንም ሥርዓት ጠብቁ።

36፤ አሮንና ልጆቹም እግዚአብሔር በሙሴ እጅ ያዘዘውን ሁሉ አደረጉ።