ምዕራፍ 3።

1፤ አሌፍ። በቍጣው በትር መከራ ያየ ሰው እኔ ነኝ።

2፤ ብርሃን ወደ ሌለበት ወደ ጨለማ መርቶ ወሰደኝ።

3፤ ዘወትር ቀኑን ሁሉ እጁን በላዬ መለሰ።

4፤ ቤት። ሥጋዬንና ቁርበቴን አስረጀ፥ አጥንቴን ሰበረ።

5፤ ቅጥር ሠራብኝ በሐሞትና በድካምም ከበበኝ።

6፤ ቀድሞ ሞተው እንደ ነበሩ በጨለማ አኖረኝ።

7፤ ጋሜል። እንዳልወጣ በዙሪያዬ ቅጥር ሠራብኝ፤ ሰንሰለቴን አከበደ።

8፤ በጠራሁና በጮኽሁ ጊዜ ጸሎቴን ከለከለ።

9፤ መንገዴን በተጠረበ ድንጋይ ዘጋ፥ ጐዳናዬንም አጣመመ።

10፤ ዳሌጥ። እንደሚሸምቅ ድብ እንደ ተሸሸገም አንበሳ ሆነብኝ።

11፤ መንገዴን ለወጠ፥ ገነጣጠለኝም፤ ባድማ አደረገኝ።

12፤ ቀስቱን ገተረ ለፍላጻውም እንደ ጊጤ አደረገኝ።

13፤ ሄ። የሰገባውን ፍላጻዎች በኵላሊቴ ውስጥ ተከለ።

14፤ ለወገኔ ሁሉ ማላገጫ ቀኑንም ሁሉ መሳለቂያ ሆንሁ።

15፤ ምሬት ሞላብኝ በእሬትም አጠገበኝ።

16፤ ዋው። ጥርሴን በጭንጫ ሰበረ፥ በአመድም ከደነኝ።

17፤ ነፍሴን ከሰላም አራቅህ፤ በጎ ነገርን ረሳሁ።

18፤ እኔም። ኃይሌ ከእግዚአብሔርም ዘንድ ያለው ተስፋዬ ጠፋ አልሁ።

19፤ ዛይ። መከራዬንና ችግሬን እሬትንና ሐሞትን አስብ።

20፤ ነፍሴ እያሰበችው በውስጤ ፈዘዘች።

21፤ ይህችን በልቤ አኖራለሁ፥ ስለዚህ እታገሣለሁ።

22፤ ሔት። ያልጠፋነው ከእግዚአብሔር ምሕረት የተነሣ ነው፤ ርኅራኄው አያልቅምና።

23፤ ማለዳ ማለዳ አዲስ ነው፤ ታማኝነትህ ብዙ ነው።

24፤ ነፍሴ። እግዚአብሔር እድል ፈንታዬ ነው፤ ስለዚህ ተስፋ አደርገዋለሁ አለች።

25፤ ጤት። እግዚአብሔር በተስፋ ለሚጠብቁት ለምትሻውም ነፍስ መልካም ነው።

26፤ ሰው ዝም ብሎ የእግዚአብሔርን ማዳን ተስፋ ቢያደርግ መልካም ነው።

27፤ ሰው በታናሽነቱ ቀንበር ቢሸከም መልካም ነው።

28፤ ዮድ። እርሱ አሸክሞታልና ዝም ብሎ ለብቻው ይቀመጥ።

29፤ ተስፋ የሆነው እንደ ሆነ አፉን በአፈር ውስጥ ያኑር።

30፤ ጕንጩን ለሚመታው ይስጥ፥ ስድብንም ይጥገብ።

31፤ ካፍ። ጌታ ለዘላለም አይጥልምና፤

32፤ ቢያሳዝንም እንደ ምሕረቱ ብዛት ይራራልና፤

33፤ የሰውን ልጆች ከልቡ አያስጨንቅም፥ አያሳዝንምም።

34፤ ላሜድ። በምድር የተጋዙትን ሁሉ ከእግሩ በታች ይረግጣቸው ዘንድ፥

35፤ የሰውን ፍርድ በልዑል ፊት ይመልስ ዘንድ፥

36፤ የሰውን ፍርድ ያጣምም ዘንድ ጌታ እሺ አይልም።

37፤ ሜም። ጌታ ያላዘዘውን የሚልና የሚፈጽም ማን ነው?

38፤ ከልዑል አፍ ክፉና መልካም ነገር አይወጣምን?

39፤ ሕያው ሰው የሚያጕረመርም፥ ሰው ስለ ኃጢአቱ ቅጣት የሚያጕረመርም ስለ ምንድር ነው?

40፤ ኖን። መንገዳችንን እንመርምርና እንፈትን፥ ወደ እግዚአብሔርም እንመለስ።

41፤ ልባችንን ከእጃችን ጋር በሰማይ ወዳለው ወደ እግዚአብሔር እናንሣ።

42፤ በድለናል ዐምፀናልም፥ አንተም ይቅር አላልህም።

43፤ ሳምኬት። በቍጣ ከደንኸን አሳደድኸንም፤ ገደልኸን፥ አልራራህም።

44፤ ጸሎት እንዳያልፍ ራስህን በደመና ከደንህ።

45፤ በአሕዛብ መካከል ጕድፍና ውዳቂ አደረግኸን።

46፤ ዔ። ጠላቶቻችን ሁሉ አፋቸውን ኣላቀቁብን።

47፤ ድንጋጤና ቍጣ፥ ጥፋትና ቅጥቃጤ ሆነብን።

48፤ ስለ ወገኔ ሴት ልጅ ቅጥቃጤ ዓይኔ የውኃ ፈሳሽ አፈሰሰች።

49፤50፤ ፌ። እግዚአብሔር ከሰማይ እስኪጐበኝና እስኪመለከት ድረስ ዓይኔ ሳታቋርጥ ዝም ሳትል እንባ ታፈስሳለች።

51፤ ስለ ከተማዬ ቈነጃጅት ሁሉ ዓይኔ ነፍሴን አሳዘነች።

52፤ ጻዴ። በከንቱ ነገር ጠላቶች የሆኑኝ እንደ ወፍ ማደንን አደኑኝ።

53፤ ሕይወቴን በጕድጓድ አጠፉ፥ በላዬም ድንጋይ ጣሉ።

54፤ በራሴ ላይ ውኆች ተከነበሉ፤ እኔም። ጠፋሁ ብዬ ነበር።

55፤ ቆፍ። አቤቱ፥ በጠለቀ ጕድጓድ ውስጥ ሆኜ ስምህን ጠራሁ።

56፤ ድምፄን ሰማህ፤ ጆሮህን ከልመናዬ አትመልስ።

57፤ በጠራሁህ ቀን ቀርበህ። አትፍራ አልህ።

58፤ ሬስ። ጌታ ሆይ፥ ስለ ነፍሴ ተምዋግተህ ሕይወቴን ተቤዠህ።

59፤ አቤቱ፥ ጭንቀቴን አይተሃል፥ ፍርዴን ፍረድልኝ።

60፤ በቀላቸውን ሁሉና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ አየህ።

61፤ ሳን። አቤቱ፥ ስድባቸውንና በእኔ ላይ ያለውን አሳባቸውን ሁሉ፥

62፤ የተነሡብኝን ሰዎች ከንፈሮች ቀኑንም ሁሉ ያሰቡብኝን አሳባቸውን ሰማህ።

63፤ መቀመጣቸውንና መነሣታቸውን ተመልከት፤ እኔ መሳለቂያቸው ነኝ።

64፤ ታው። አቤቱ፥ እንደ እጃቸው ሥራ ፍዳቸውን ትከፍላቸዋለህ።

65፤ የልብ ዕውርነትንና እርግማንህን ትሰጣቸዋለህ።

66፤ አቤቱ፥ በቍጣ ታሳድዳቸዋለህ ከሰማይም በታች ታጠፋቸዋለህ።