ምዕራፍ 16።

1፤ የዮሴፍም ልጆች ዕጣ በኢያሪኮ አጠገብ በምሥራቁ በኩል ካለው ከዮርዳኖስ አንሥቶ በምድረ በዳውና በተራራማው በኩል ከኢያሪኮ ወደ ቤቴል ወጣ፤

2፤ ከቤቴል ወደ ሎዛ ወጣ፥ በአርካውያንም ዳርቻ በኩል ወደ አጣሮት አለፈ፥

3፤ ወደ ምዕራብም እስከ የፍሌጣውያን ዳርቻ እስከ ታችኛው ቤትሖሮን ዳርቻ እስከ ጌዝር ድረስ ወረደ፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ።

4፤ የዮሴፍም ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ርስታቸውን ወረሱ።

5፤ የኤፍሬምም ልጆች ድንበር በየወገኖቻቸው እንደዚህ ነበረ፤ በምሥራቅ በኩል የርስታቸው ድንበር አጣሮትአዳር እስከ ላይኛው ቤትሖሮን ድረስ ነበረ፤

6፤ ድንበሩም ወደ ምዕራብ ወደ ሚክምታት በሰሜን በኩል ወጣ፤ ድንበሩም ወደ ምሥራቅ ወደ ተአናትሴሎ ዞረ፥ ወደ ኢያኖክ በምሥራቅ በኩል አለፈ፥

7፤ ከኢያኖክም ወደ አጣሮትና ወደ ነዓራት ወረደ፤ ወደ ኢያሪኮም ደረሰ፥ ወደ ዮርዳኖስም ወጣ።

8፤ ድንበሩም ከታጱዋ ወደ ምዕራብ እስከ ቃና ወንዝ ድረስ አለፈ፥ መውጫውም በባሕሩ አጠገብ ነበረ። የኤፍሬም ልጆች ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው ይህ ነበረ።

9፤ ይኸውም በምናሴ ልጆች ርስት መካከል ለኤፍሬም ልጆች ከተለዩ ከተሞች ጋር፥ ከተሞች ሁሉ ከመንደሮቻቸው ጋር፥ ነው።

10፤ በጌዝርም የተቀመጡትን ከነዓናውያንን አላሳደዱአቸውም፥ እስከ ዛሬም ድረስ ከነዓናውያን በኤፍሬም መካከል ተቀምጠዋል፤ የጕልበት ግብርም ያስገብሩአቸው ነበር። a