ምዕራፍ 9።

1፤ እንዲህም ሆነ፤ በዮርዳኖስ ማዶ በተራራማው በቈላውም በታላቁ ባሕር ዳር በሊባኖስም ፊት ለፊት የነበሩ ነገሥታት ሁሉ፥ ኬጢያዊ አሞራዊም ከነዓናዊም ፌርዛዊም ኤዊያዊም ኢያቡሳዊም፥ ይህን በሰሙ ጊዜ፥

2፤ ኢያሱንና እስራኤልን ሊወጉ አንድ ሆነው ተሰበሰቡ።

3፤ የገባዖን ሰዎች ግን ኢያሱ በኢያሪኮና በጋይ ያደረገውን በሰሙ ጊዜ፥

4፤ እነርሱ ደግሞ ተንኰል አደረጉ፤ ለራሳቸውም ስንቅ ያዙ፥ በአህዮቻቸውም ላይ አሮጌ ዓይበትና ያረጀና የተቀደደ የተጠቀመም የጠጅ አቁማዳ ጫኑ።

5፤ ያረጀ የተጠቀመም ጫማ በእግራቸው አደረጉ አሮጌም ልብስ ለበሱ፤ ለስንቅም የያዙት እንጀራ ሁሉ የደረቀና የሻገተ ነበረ።

6፤ ኢያሱም ወደ ሰፈረበት ወደ ጌልገላ ሄደው ለእርሱና ለእስራኤል ሰዎች። ከሩቅ አገር መጥተናል፤ አሁንም ከእኛ ጋር ኪዳን አድርጉ አሉ።

7፤ የእስራኤልም ሰዎች ኤዊያውያንን። ምናልባት በመካከላችን የምትቀመጡ እንደ ሆነ እንዴትስ ከእናንተ ጋር ቃል ኪዳን እናደርጋለን? አሉአቸው።

8፤ ኢያሱንም። እኛ ባሪያዎችህ ነን አሉት። ኢያሱም። እናንተ እነማን ናችሁ? ከወዴትስ መጣችሁ? አላቸው።

9፤ እነርሱም አሉት። ከአምላክህ ከእግዚአብሔር ስም የተነሣ እጅግ ከራቀ አገር ባሪያዎችህ መጥተናል፤ ዝናውንም፥ በግብፅም ያደረገውን ሁሉ፥

10፤ በዮርዳኖስ ማዶም በነበሩት በሁለቱ በአሞራውያን ነገሥታት በሐሴቦን ንጉሥ በሴዎን በአስታሮትም በነበረው በባሳን ንጉሥ በዐግ ያደረገውን ሁሉ ሰምተናል።

11፤ ሽማግሌዎቻችንም በምድራችንም የሚኖሩት ሁሉ። ለመንገድ ስንቅ በእጃችሁ ያዙ፥ ልትገናኙአቸውም ሂዱ። እኛ ባሪያዎቻችሁ ነን፤ አሁንም ከእኛ ጋር ቃል ኪዳን አድርጉ በሉአቸው አሉን።

12፤ ወደ እናንተ ለመምጣት በተነሣንበት ቀን ይህን እንጀራ ትኩሱን ለስንቅ ከቤታችን ወሰድነው፤ አሁንም እነሆ፥ ደርቆአል፥ ሻግቶአልም።

13፤ እነዚህም የጠጅ አቁማዳዎች አዲስ ሳሉ ሞላንባቸው፤ እነሆም፥ ተቀድደዋል፤ መንገዳችንም እጅግ ስለ ራቀብን እነዚህ ልብሶቻችንና ጫማዎቻችን አርጅተዋል።

14፤ ሰዎቹም ከስንቃቸው ወሰዱ፥ እግዚአብሔርንም አልጠየቁም።

15፤ ኢያሱም ከእነርሱ ጋር ሰላም አደረገ፥ በሕይወት እንዲተዋቸውም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ የማኅበሩም አለቆች ማሉላቸው።

16፤ ከእነርሱም ጋር ቃል ኪዳን ካደረጉ ከሦስት ቀን በኋላ ጎረቤቶቻቸው እንደ ሆኑ በመካከላቸውም እንደ ኖሩ ሰሙ።

17፤ የእስራኤልም ልጆች ተጕዘው በሦስተኛው ቀን ወደ ከተሞቻቸው መጡ፤ የከተሞቻቸውም ስም ገባዖን፥ ከፊራ፥ ብኤሮት፥ ቂርያትይዓሪም ነበረ።

18፤ የሕዝቡም አለቆች በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስለ ማሉላቸው የእስራኤል ልጆች አልመቱአቸውም። ማኅበሩም ሁሉ በአለቆቹ ላይ አጕረመረሙ።

19፤ አለቆቹም ሁሉ ለማኅበሩ ሁሉ። በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ምለንላቸዋል፤ ስለዚህም እንነካቸው ዘንድ አይገባንም።

20፤ ስለ ማልንላቸው መሓላ ቍጣ እንዳይወርድብን ይህን እናድርግባቸው፥ በሕይወትም እንተዋቸው አሉአቸው።

21፤ አለቆቹም። በሕይወት ይኑሩ አሉአቸው፤ አለቆቹም እንደ ተናገሩአቸው ለማኅበሩ ሁሉ እንጨት ቆራጮች ውኃም ቀጂዎች ሆኑ።

22፤ ኢያሱም ጠርቶ። እናንተ በመካከላችን ስትኖሩ። ከእናንተ እጅግ የራቅን ነን ብላችሁ ለምን አታለላችሁን?

23፤ አሁንም የተረገማችሁ ናችሁ፤ ለአምላኬም ቤት እንጨት ቈራጭ ውኃም ቀጂ የሆነ ባሪያ ከእናንተ ለዘላለም አይጠፋም አላቸው።

24፤ መልሰውም ኢያሱን። እኛ ባሪያዎችህ ምድሪቱን ሁሉ ይሰጣችሁ ዘንድ፥ በእርስዋም የሚኖሩትን ሁሉ ከፊታችሁ ያጠፋ ዘንድ አምላክህ እግዚአብሔር ባሪያውን ሙሴን እንዳዘዘ በእውነት ሰምተናል፥ ስለዚህም ከእናንተ የተነሣ ስለ ነፍሳችን እጅግ ፈራን፥ ይህንንም ነገር አድርገናል።

25፤ አሁንም፥ እነሆ፥ በእጅህ ውስጥ ነን፤ ለዓይንህም መልካምና ቅን የመሰለውን ነገር አድርግብን አሉት።

26፤ እንዲሁም አደረገባቸው፥ ከእስራኤልም ልጆች እጅ አዳናቸው፥ አልገደሉአቸውምም።

27፤ በዚያም ቀን ኢያሱ ለማኅበሩ በመረጠውም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ ለእግዚአብሔር መሠዊያ እንጨት ቈራጮች ውኃም ቀጂዎች አደረጋቸው።