ምዕራፍ 17

1-2 ኢየሱስም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ ዓይኖቹን አነሣና እንዲህ አለ። አባት ሆይ፥ ሰዓቱ ደርሶአል፤ ልጅህ ያከብርህ ዘንድ፥ በሥጋም ሁሉ ላይ ሥልጣን እንደ ሰጠኸው፥ ለሰጠኸው ሁሉ የዘላለምን ሕይወት ይሰጣቸው ዘንድ ልጅህን አክብረው።

3 እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህ አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት።

4 እኔ ላደርገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ፤

5 አሁንም፥ አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር በአንተ ዘንድ በነበረኝ ክብር አንተ በራስህ ዘንድ አክብረኝ።

6 ከዓለም ለሰጠኸኝ ሰዎች ስምህን ገለጥሁላቸው። የአንተ ነበሩ ለእኔም ሰጠሃቸው፤

7 ቃልህንም ጠብቀዋል። የሰጠኸኝ ሁሉ ከአንተ እንደ ሆነ አሁን ያውቃሉ፤

8 የሰጠኸኝን ቃል ሰጥቻቸዋለሁና፤ እነርሱም ተቀበሉት፥ ከአንተም ዘንድ እንደ ወጣሁ በእውነት አወቁ፥ አንተም እንደ ላክኸኝ አመኑ።

9 እኔ ስለ እነዚህ እለምናለሁ፤ ስለ ዓለም አልለምንም ስለ ሰጠኸኝ እንጂ፤ የአንተ ናቸውና፤

10 የእኔም የሆነ ሁሉ የአንተ ነው የአንተውም የእኔ ነው፤ እኔም ስለ እነርሱ ከብሬአለሁ።

11 ከዚህም በኋላ በዓለም አይደለሁም፥ እነርሱም በዓለም ናቸው፥ እኔም ወደ አንተ እመጣለሁ። ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው።

12 ከእነርሱ ጋር በዓለም ሳለሁ የሰጠኸኝን በስምህ እኔ እጠብቃቸው ነበር፤ ጠበቅኋቸውም መጽሐፉም እንዲፈጸም ከጥፋት ልጅ በቀር ከእነርሱ ማንም አልጠፋም።

13 አሁንም ወደ አንተ እመጣለሁ፤ በእነርሱም ዘንድ ደስታዬ የተፈጸመ እንዲሆንላቸው ይህን በዓለም እናገራለሁ።

14 እኔ ቃልህን ሰጥቻቸዋለሁ፤ እኔም ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉምና ዓለም ጠላቸው።

15 ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አልለምንም።

16 እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።

17 በእውነትህ ቀድሳቸው፤ ቃልህ እውነት ነው።

18 ወደ ዓለም እንደ ላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤

19 እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንዲሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ።

20-21 ሁሉም አንድ ይሆኑ ዘንድ፥ ከቃላቸው የተነሣ በእኔ ስለሚያምኑ ደግሞ እንጂ ስለ እነዚህ ብቻ አልለምንም፤ አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምን ዘንድ፥ አንተ፥ አባት ሆይ፥ በእኔ እንዳለህ እኔም በአንተ፥ እነርሱ ደግሞ በእኛ አንድ ይሆኑ ዘንድ እለምናለሁ።

22-23 እኛም አንድ እንደ ሆንን አንድ ይሆኑ ዘንድ፤ እኔም በእነርሱ አንተም በእኔ ስትሆን፥ በአንድ ፍጹማን እንዲሆኑ፥ የሰጠኸኝን ክብር እኔ ሰጥቻቸዋለሁ፤ እንዲሁም ዓለም አንተ እንደ ላክኸኝ በወደድኸኝም መጠን እነርሱን እንደ ወደድሃቸው ያውቃል።

24 አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ።

25 ጻድቅ አባት ሆይ፥ ዓለም አላወቀህም፥ እኔ ግን አወቅሁህ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤

26 እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን እኔም በእነርሱ፥ ስምህን አስታወቅኋቸው አስታውቃቸውማለሁ።