ምዕራፍ 1።

1፤ ወደ ባቱኤል ልጅ ወደ ኢዩኤል የመጣው የእግዚአብሔር ቃል ይህ ነው።

2፤ እናንተ ሽማግሌዎች፥ ይህን ስሙ፤ በምድርም የምትኖሩ ሁሉ፥ አድምጡ። ይህ በዘመናችሁ ወይስ በአባቶቻችሁ ዘመን ሆኖ ነበርን?

3፤ ይህን ለልጆቻችሁ ንገሩ፤ ልጆቻችሁም ለልጆቻቸው፥ ልጆቻቸውም ለኋለኛው ትውልድ ይንገሩ።

4፤ ከተሞች የቀረውን አንበጣ በላው፤ ከአንበጣም የቀረውን ደጎብያ በላው፤ ከደጎብያም የቀረውን ኩብኩባ በላው።

5፤ በተሃ ወይን ጠጃችሁ ከአፋችሁ ተወግዶአልና እናንተ ሰካራሞች፥ ነቅታችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የወይን ጠጅ የምትጠጡ ሁሉ፥ ዋይ በሉ።

6፤ ቍጥርም የሌለው ብርቱ ሕዝብ በምድሬ ላይ ወጥቶአልና፤ ጥርሳቸው እንደ አንበሳ ጥርስ፥ መንጋጋቸውም እንደ እንስቲቱ አንበሳ መንጋጋ ነው።

7፤ ወይኔን ባዶ ምድር አደረገው፥ በለሴንም ሰበረው፤ ባዶም አደረገው፥ ጣለውም፤ ቅርንጫፎቹም ነጡ።

8፤ ለቍንጅናዋ ባል ማቅ ለብሳ እንደምታለቅስ ድንግል አልቅሺ።

9፤ የእህሉ ቍርባንና የመጠጡ ቍርባን ከእግዚአብሔር ቤት ተወግዶአል፤ የእግዚአብሔርም አገልጋዮች ካህናቱ አለቀሱ።

10፤ እህሉ ጠፍቶአልና፥ ወይኑም ደርቆአልና፥ ዘይቱም ጐድሎአልና እርሻው ምድረ በዳ ሆኖአል፥ ምድሪቱም አልቅሳለች።

11፤ መከሩ ከእርሻቸው ጠፍቶአልና ገበሬዎች ስለ ስንዴውና ስለ ገብሱ አፈሩ፤ የወይን አትክልተኞችም አለቀሱ።

12፤ ወይኑ ደርቆአል፥ በለሱም ጠውልጎአል፤ ሮማኑና ተምሩ እንኰዩም የምድርም ዛፎች ሁሉ ደርቀዋል፤ ደስታም ከሰው ልጆች ዘንድ ርቆአል።

13፤ የእህሉ ቍርባንና የመጠጡ ቍርባን ከአምላካችሁ ቤት ቀርቶአልና እናንተ ካህናት፥ ማቅ ታጥቃችሁ አልቅሱ፤ እናንተም የመሠዊያ አገልጋዮች፥ ዋይ በሉ፤ እናንተ የአምላኬ አገልጋዮች፥ ኑ፥ ሌሊቱን ሁሉ በማቅ ላይ ተኙ።

14፤ ጾምን ቀድሱ፥ ጉባኤውንም አውጁ፤ ሽምግሌዎችንና በምድር የሚኖሩትን ሁሉ ወደ አምላካችሁ ወደ እግዚአብሔር ቤት ሰብስቡ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጩኹ።

15፤ የእግዚአብሔር ቀን ቀርቦአልና ለቀኑ ወዮ! እርሱም ሁሉን ከሚችል ከአምላክ ዘንድ እንደ ጥፋት ይመጣል።

16፤ ከዓይናችን ፊት ምግብ፥ ከአምላካችንም ቤት ደስታና እልልታ የጠፋ አይደለምን?

17፤ ዘሩ በምድር ውስጥ በሰበሰ፤ እህሉ ደርቆአልና ጎተራዎቹ ባዶ ናቸው፥ ጎታዎቹም ፈርሰዋል።

18፤ እንስሶች እጅግ ጮኹ፤ የላምም መንጎች ማሰማርያ የላቸውምና ተጠራጠሩ፤ የበግም መንጎች ጠፍተዋል።

19፤ አቤቱ፥ እሳት የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና፥ ነበልባሉም የዱሩን ዛፍ ሁሉ አቃጥሎአልና ወደ አንተ እጮኻለሁ።

20፤ ፈሳሹ ውኃ ደርቆአልና፥ እሳቱም የምድረ በዳውን ማሰማርያ በልቶአልና የምድር አራዊት ወደ አንተ አለኸለኩ።