ምዕራፍ 32።

1፤ ኢዮብም ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና እነዚያ ሦስቱ ሰዎች መመለስን ተዉ።

2፤ ከራም ወገን የሆነ የቡዛዊው የባርክኤል ልጅ የኤሊሁ ቍጣ ነደደ፤ ከእግዚአብሔር ይልቅ ራሱን ጻድቅ አድርጎ ነበርና ኢዮብን ተቈጣው።

3፤ ደግሞም በኢዮብ ፈረዱበት እንጂ የሚገባ መልስ ስላላገኙ በሦስቱ ባልንጀሮቹ ላይ ተቈጣ።

4፤ ኤሊሁ ግን ከእርሱ ይልቅ ሽማግሌዎች ነበሩና ከኢዮብ ጋር መናገርን ጠብቆ ነበር።

5፤ ኤሊሁም በነዚህ በሦስቱ ሰዎች አፍ መልስ እንደሌለ ባየ ጊዜ ቍጣው ነደደ።

6፤ የቡዛዊውም የባርክኤል ልጅ ኤሊሁ ተናገረ እንዲህም አለ።

እኔ በዕድሜ ታናሽ ነኝ፥ እናንተ ግን ሽማግሌዎች ናችሁ፤

ስለዚህም ሰጋሁ፤ እውቀቴን እገልጥላችሁ ዘንድ ፈራሁ።

7፤ እንደዚህም አልሁ። ዓመታት በተናገሩ ነበር፥

የዓመታትም ብዛት ጥበብን ባስተማረች ነበር።

8፤ ነገር ግን በሰው ውስጥ መንፈስ አለ፥

ሁሉንም የሚችል የአምላክ እስትንፋስ ማስተዋልን ይሰጣል።

9፤ በዕድሜ ያረጁ ጠቢባን አይደሉም፥

ሽማግሌዎችም ፍርድን አያስተውሉም።

10፤ ስለዚህም። ስሙኝ፤

እኔ ደግሞ እውቀቴን እገልጥላችኋለሁ አልሁ።

11፤ እነሆ፥ ቃላችሁን በትዕግሥት ጠበቅሁ፤

የምትናገሩትን ነገር እስክትመረምሩ ድረስ፤

ብልሃታችሁን አዳመጥሁ።

12፤ እንዲሁም ልብ አደረግሁ፤

እነሆም፥ በእናንተ መካከል ኢዮብን ያስረዳ፥

ወይም ለቃሉ የመለሰ የለም።

13፤ እናንተም። ጥበብን አግኝተናል፤

እግዚአብሔር ነው እንጂ ሰው አያሸንፈውም እንዳትሉ ተጠንቀቁ።

14፤ እርሱ ግን ቃሉን በእኔ ላይ አልተናገረም፤

እኔም በንግግራችሁ አልመልስለትም።

15፤ እነርሱ ደነገጡ፥ ዳግመኛም አልመለሱም፤

የሚናገሩትንም አጡ።

16፤ እነርሱ አልተናገሩምና፥

ቆመው ዳግመኛ አልመለሱምና እኔ በትዕግሥት እጠብቃለሁን?

17፤ እኔ ደግሞ ፈንታዬን እመልሳለሁ፥

እውቀቴንም እገልጣለሁ፤

18፤ እኔ ቃል ተሞልቻለሁና፥

በውስጤም ያለ መንፈስ አስገድዶኛልና።

19፤ በተሐ ጠጅ እንደ ተሞላና ሊቀደድ እንደ ቀረበ አቁማዳ፥

ሊፈነዳ እንደማይችል እንደ ወይን ጠጅ

አቁማዳ፥ እነሆ፥ አንጀቴ ሆነ።

20፤ ጥቂት እንድተነፍስ እናገራለሁ፤

ከንፈሬን ገልጬ እመልሳለሁ።

21፤ ለሰው ፊት ግን አላደላም፤

ሰውንም አላቈላምጥም።

22፤ በማቈላመጥ እናገር ዘንድ አላውቅምና፤

ያለዚያስ ፈጣሪዬ ፈጥኖ ከሕይወቴ ይለየኝ ነበር።