ምዕራፍ 30።

1፤ አሁን ግን በዕድሜ ከእኔ የሚያንሱ፥

አባቶቻቸውን ከመንጋዬ ውሾች ጋር ለማኖር የናቅኋቸው፥

በእኔ ላይ ተሳለቁብኝ።

2፤ ሙሉ ሰው መሆናቸው ጠፍቶባቸው ነበርና

የእጃቸው ብርታት ለእኔ ምን ይጠቅማል?

3፤ በራብና በቀጠና የመነመኑ ናቸው፤

የመፍረስና የመፈታት ጨለማ ወዳለበት

ወደ ምድረ በዳ ይሸሻሉ።

4፤ በቍጥቋጦ አጠገብ ያለውን

ጨው ጨው የሚለውን አትክልት ይለቅማሉ፤

የክትክታ ሥር ደግሞ መብላቸው ነው።

5፤ ከሰዎች ተለይተው ተሰደዱ፤

በሌባ ላይ እንደሚጮኽ ይጮኹባቸዋል።

6፤ በሸለቆ ፈረፈርና በምድር ጕድጓድ

በድንጋይም ዋሻ ውስጥ ይኖራሉ።

7፤ በቍጥቋጦ መካከል ይጮኻሉ፤

ከሳማ በታች ተሰብስበዋል።

8፤ የሰነፎችና የነውረኞች ልጆች ናቸው፤

ከምድርም በግርፋት የተባረሩ ናቸው።

9፤ አሁንም እኔ መዝፈኛና መተረቻ ሆንኋቸው።

10፤ ተጸየፉኝ፥ ከእኔም ራቁ፤

አክታቸውንም በፊቴ መትፋትን አልተዉም።

11፤ የቀስቴን አውታር አላልቶብኛል፥ አዋርዶኝማል፤

እነርሱም በፊቴ ልጓማቸውን ፈትተዋል።

12፤ በቀኜ በኩል ዱርዬዎች ተነሥተዋል፥

እግሬንም ይገለብጣሉ፤

የጥፋታቸውን መንገድ በእኔ ላይ ይጐድባሉ።

13፤ ጐዳናዬን ያበላሻሉ፤

ረዳት የሌላቸው ሰዎች መከራዬን ያበዛሉ።

14፤ በሰፊ ፍራሽ እንደሚመጡ ይመጡብኛል፤

በባድማ ውስጥ ይንከባለሉብኛል።

15፤ ድንጋጤ በላዬ ተመለሰችብኝ፥

ክብሬንም እንደ ነፋስ ያሳድዱአታል፤

ደኅንነቴም እንደ ደመና አልፋለች።

16፤ አሁንም ነፍሴ በውስጤ ፈሰሰች፤

የመከራም ዘመን ያዘችኝ።

17፤ በሌሊት አጥንቴ በደዌ ተነደለች፥

ጅማቶቼም አያርፉም።

18፤ ከታላቁ ደዌ ኃይል የተነሣ ልብሴ ተበላሸች፤

እንደ ቀሚስ ክሳድ አነቀችኝ።

19፤ እርሱ በጭቃ ውስጥ ጣለኝ፥

አፈርና አመድም መሰልሁ።

20፤ ወደ አንተ ጮኽሁ፥ አልመለስህልኝም፤

ተነሣሁ፥ አልተመለከትኸኝም።

21፤ ተመልሰህ ጨካኝ ሆንህብኝ፤

በእጅህም ብረታት አስጨነቅኸኝ።

22፤ በነፋስ አነሣኸኝ፥ በላዩም አስቀመጥኸኝ፤

በዐውሎ ነፋስ አቀለጥኸኝ።

23፤ ለሞት ሕያዋንም ሁሉ ለሚሰበሰቡበት ቤት አሳልፈህ እንደምትሰጠኝ አውቄአለሁና።

24፤ ነገር ግን ሰው በወደቀ ጊዜ እጁን አይዘረጋምን?

በጥፋቱስ ጊዜ አይጮኽምን?

25፤ ጭንቅ ቀን ላገኘው ሰው አላለቀስሁምን?

ለችግረኛስ ነፍሴ አላዘነችምን?

26፤ ነገር ግን በጎነትን በተጠባበቅሁ ጊዜ ክፉ ነገር መጣችብኝ፤

ብርሃንን በትዕግሥት ጠበቅሁ፥ ጨለማም መጣ።

27፤ አንጀቴ ፈላች፥ አላረፈችም፤

የመከራም ዘመን መጣችብኝ።

28፤ ያለ ፀሐይ በትካዜ ሄድሁ፤

በጉባኤም መካከል ቆሜ ጮኽሁ።

29፤ ለቀበሮ ወንድም፥

ለሰጐንም ባልንጀራ ሆንሁ።

30፤ ቁርበቴ ጠቈረ፥ ከእኔም ተለይቶ እርግፍግፍ አለ፤

አጥንቴም ከትኵሳት የተነሣ ተቃጠለች።

31፤ ስለዚህ መሰንቆዬ ለኀዘን፥

እምቢልታዬም ለሚያለቅሱ ቃል ሆነ።