ምዕራፍ 25።

1፤ ሹሐዊውም በልዳዶስ መለሰ እንዲህም አለ።

2፤ ገዢነትና መፈራት በእርሱ ዘንድ ናቸው፤

በከፍታውም ሰላም አድራጊ ነው።

3፤ በውኑ ለሠራዊቶቹ ቍጥር አላቸውን?

ብርሃኑስ የማይወጣው በማን ላይ ነው?

4፤ ሰውስ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ይሆን ዘንድ፥

ከሴትስ የተወለደ ንጹሕ ይሆን ዘንድ እንዴት ይችላል?

5፤ እነሆ፥ ጨረቃ እንኳ ብሩህ አይደለም፥

ከዋክብትም በፊቱ ንጹሐን አይደሉም።

6፤ ይልቁንስ ብስብስ የሆነ ሰው፥

ትልም የሆነ የሰው ልጅ ምንኛ ያንስ!