ምዕራፍ 21

1 ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ ኤርምያስ የመጣ ቃል ይህ ነው።

2 ይህም የሆነው ንጉሡ ሴዴቅያስ። የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ይወጋናልና ስለ እኛ፥ እባክህ፥ እግዚአብሔርን ጠይቅ፤ ከእኛም ይመለስ ዘንድ ምናልባት እግዚአብሔር ከእኛ ጋር እንደ ተአምራቱ ሁሉ ያደርግ ይሆናል ብሎ የመልክያን ልጅ ጳስኮርንና ካህኑን የመዕሤያን ልጅ ሶፎንያስ ወደ ኤርምያስ በላከ ጊዜ ነው።

3 ኤርምያስም እንዲህ አላቸው። ሴዴቅያስን እንዲህ በሉት።

4 የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የባቢሎንን ንጉሥ በቅጥርም ውጭ የከበቡአችሁን ከለዳውያንን የምትወጉበትን በእጃችሁ ያለውን ዕቃ ጦራችሁን እመልሰዋለሁ፥ እነዚያንም ወደዚህች ከተማ ውስጥ እሰበስባቸዋለሁ።

5 እኔም በተዘረጋች እጅና በብርቱ ክንድ፥ በቍጣና በመዓት በታላቅም መቅሠፍት እወጋችኋለሁ።

6 በዚህችም ከተማ የሚኖሩትን ሁሉ ሰዎችንና እንስሶችን እመታለሁ፥ በጽኑም ቸነፈር ይሞታሉ።

7 ከዚህ በኋላ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ የይሁዳን ንጉሥ ሴዴቅያስን ከቸነፈርና ከሰይፍ ከራብም በዚህች ከተማ የቀሩትንም ባሪዎቹንና ሕዝቡን በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆር እጅ በጠላቶቻቸውና ነፍሳቸውንም በሚሹት እጅ አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ እርሱም በሰይፍ ስለት ይመታቸዋል፤ አያዝንላቸውም፥ አይራራላቸውም፥ አይምራቸውም።

8 ለዚህም ሕዝብ እንዲህ በል። እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ በፊታችሁ የሕይወትን መንገድና የሞትን መንገድ አድርጌአለሁ።

9 በዚህች ከተማ ውስጥ የሚዘገይ በሰይፍና በራብ በቸነፈርም ይሞታል፤ ወጥቶ ወደ ከበቡአችሁ ወደ ከለዳውያን የሚገባ ግን በሕይወት ይኖራል፥ ነፍሱም ምርኮ ትሆንለታለች።

10 ለመልካም ሳይሆን ለክፋ ፊቴን በዚህች ከተማ ላይ አድርጌአለሁና፤ ለባቢሎን ንጉሥ እጅ ትሰጣለች፥ እርሱም በእሳት ያቃጥላታል።

11 የይሁዳ ንጉሥ ቤት ሆይ፥ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

12 የዳዊት ቤት ሆይ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ ሥራችሁ ክፋት ቍጣዬ እንደ እሳት እንዳይወጣና ማንም ሳያጠፋው እንዳይነድድ፥ በማለዳ ፍርድን አድርጉ የተበዘበዘውንም ከአስጨናቂው እጅ አድኑ።

13 እነሆ፥ በሸለቆው ውስጥ በሜዳ ላይም ባለው አምባ የምትቀመጪ ሆይ፥ እኔ በአንቺ ላይ ነኝ፤ እናንተም። በእኛ ላይ የሚወርድ ወይም ወደ መኖሪያችን የሚገባ ማን ነው? የምትሉ ሆይ፥ እኔ በእናንተ ላይ ነኝ፤

14 እንደ ሥራችሁም ፍሬ እቀጣችኋለሁ፤ በዱርዋም ውስጥ እሳትን አነድዳለሁ፥ በዙሪያዋም ያለውን ሁሉ ይበላል።