ምዕራፍ 43።

1፤ አሁንም ያዕቆብ ሆይ፥ የፈጠረህ፥ እስራኤልም ሆይ፥ የሠራህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ተቤዥቼሃለሁና አትፍራ፤ በስምህም ጠርቼሃለሁ፥ አንተ የእኔ ነህ።

2፤ በውኃ ውስጥ ባለፍህ ጊዜ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፥ በወንዞችም ውስጥ ባለፍህ ጊዜ አያሰጥሙህም፤ በእሳትም ውስጥ በሄድህ ጊዜ አትቃጠልም፥ ነበልባሉም አይፈጅህም።

3፤ እኔ የእስራኤል ቅዱስ አምላክህ እግዚአብሔር መድኃኒትህ ነኝ፤ ግብጽን ለአንተ ቤዛ አድርጌ፥ ኢትዮጵያንና ሳባንም ለአንተ ፋንታ ሰጥቻለሁ።

4፤ በዓይኔ ፊት የከበርህና የተመሰገንህ ነህና፥ እኔም ወድጄሃለሁና ስለዚህ ሰዎችን ለአንተ አሕዛብንም ለነፍስህ እሰጣለሁ።

5፤ እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ ዘርህንም ከምሥራቅ አመጣዋለሁ፥ ከምዕራብም እሰበስብሃለሁ።

6፤7፤ ሰሜንን። መልሰህ አምጣ፥ ደቡብንም። አትከልክል፤ ወንዶች ልጆቼን ከሩቅ ሴቶች ልጆቼንም ከምድር ዳርቻ፥ በስሜ የተጠራውን ለክብሬም የፈጠርሁትን፥ የሠራሁትንና ያደረግሁትን ሁሉ አምጣ እለዋለሁ።

8፤ ዓይኖች ያሉአቸውን ዕውሮችን ሕዝብ፥ ጆሮችም ያሉአቸውን ደንቆሮቹን አውጣ።

9፤ አሕዛብ ሁሉ በአንድነት ይሰብሰቡ ወገኖችም ይከማቹ፤ ከመካከላቸው፤ ይህን የሚናገር፥ የቀድሞውንስ ነገር የሚያሳየን ማን ነው? ይጸድቁ ዘንድ ምስክሮቻቸውን ያምጡ፥ ሰምተውም እውነት ነው ይበሉ።

10፤ ታውቁና ታምኑብኝ ዘንድ እኔም እንደሆንሁ ታስተውሉ ዘንድ፥ እናንተ የመረጥሁትም ባሪያዬ ምስክሮቼ ናችሁ ይላል እግዚአብሔር፤ ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም ከእኔም በኋላ አይሆንም።

11፤ እኔ፥ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከእኔ ሌላም የሚያድን የለም።

12፤ ተናግሬአለሁ አድኜማለሁ አሳይቼማለሁ፥ በእናንተም ዘንድ ባዕድ አምላክ አልነበረም፤ ስለዚህ እናንተ ምስክሮቼ ናችሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፥ እኔም አምላክ ነኝ።

13፤ ከጥንት ጀምሮ እኔ ነኝ ከእጄም የሚያመልጥ የለም፤ እሠራለሁ፥ የሚከለክልስ ማን ነው?

14፤ የእስራኤል ቅዱስ፥ የሚቤዣችሁ፥ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ስለ እናንተ ወደ ባቢሎን ሰድጃለሁ፥ ከለዳውያንንም ሁሉ ስደተኞች አድርጌ በሚመኩባቸው መርከቦች አዋርዳቸዋለሁ።

15፤ ቅዱሳችሁ፥ የእስራኤል ፈጣሪ፥ ንጉሣችሁ፥ እግዚአብሔር እኔ ነኝ።

16፤ እግዚአብሔር በባሕር ውስጥ መንገድን በኃይለኛም ውኃ ውስጥ መተላለፊያን ያደርጋል፤

17፤ እግዚአብሔር ሰረገላውንና ፈረሱን ሠራዊቱንና አርበኛውን ያወጣል፤ እነርሱ ግን በአንድነት ተኝተዋል፥ አይነሡም፤ ቀርተዋል፥ እንደ ጥዋፍ ኩስታሪም ጠፍተዋል፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።

18፤ የፊተኛውን ነገር አታስተውሉ፥ የጥንቱንም ነገር አታስቡ።

19፤ እነሆ፥ አዲስ ነገርን አደርጋለህ፤ እርሱም አሁን ይበቅላል፥ እናንተም አታውቁትምን? በምድረ በዳም መንገድን በበረሀም ወንዞችን አደርጋለሁ።

20፤21፤ ምስጋናዬን እንዲናገሩ ለእኔ የፈጠርሁት ሕዝብ፥ የመረጥሁትን ሕዝቤን አጠጣ ዘንድ በምድረ በዳ ውኃን በበረሀም ወንዞችን ሰጥቻለሁና የምድረ በዳ አራዊት፥ ቀበሮችና ሰጎኖች፥ ያከብሩኛል።

22፤ ያዕቆብ ሆይ፥ አንተ ግን አልጠራኸኝም፥ አንተም እስራኤል ሆይ፥ በእኔ ዘንድ ደክመሃል።

23፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት በጎችህን አላቀረብህልኝም በሌላም መሥዋዕትህ አላከበርኸኝም፤ በእህልም ቍርባን አላስቸገርሁህም በዕጣንም አላደከምሁህም።

24፤ ዕጣንም በገንዘብ አልገዛህልኝም በመሥዋዕትህም ስብ አላጠገብኸኝም፤ ነገር ግን በኃጢአትህ አስቸገርኸኝ፥ በበደልህም አደከምኸኝ።

25፤ መተላለፍህን። ስለ እኔ ስል የምደመስስ እኔ ነኝ፤ ኃጢአትህንም አላስብም።

26፤ አሳስበኝ፥ በአንድነትም ሆነን እንፋረድ፤ እንድትጸድቅ ነገርህን ተናገር።

27፤ ፊተኛው አባትህ ኃጢአት ሠርቶአል፥ መምህሮችህም በድለውኛል።

28፤ ስለዚህ የመቅደሱን አለቆች አረከስሁ፥ ያዕቆብንም እርግማን፥ እስራኤልንም ስድብ አደረግሁ።