ምዕራፍ 16።

1፤ በምድርም ላይ ለሠለጠነው አለቃ የበግ ጠቦቶችን በምድረ በዳ ካለችው ከሴላ ወደ ጽዮን ሴት ልጅ ተራራ ስደዱ።

2፤ እንደሚበርር ወፍ እንደ ተበተኑም ጫጩቶች እንዲሁ የሞዓብ ሴቶች ልጆች በአርኖን መሻገሪያዎች ይሆናሉ።

3፤ ምክርን ምከሪ፥ ፍርድን አድርጊ፥ በቀትር ጊዜ ጥላሽን እንደ ሌሊት አድርጊ፤ የተሰደዱትን ሸሽጊ፥ የሸሹትን አትግለጪ።

4፤ ከሞዓብ የተሰደዱት ከአንቺ ጋር ይቀመጡ፤ ከሚያጠፋቸው ፊት መጋረጃ ሁኛቸው። የሚያስጨንቁ አልቀዋል፥ ጥፋትም ቀርቶአል፤ ይጨቍኑ የነበሩ ከምድር ጠፍተዋል።

5፤ ዙፋንም በምሕረት ይቀናል፥ በዚያም ላይ በዳዊት ድንኳን ፍርድን የሚሻ ጽድቅንም የሚያፈጥን ፈራጅ በእውነት ይቀመጣል

6፤ ስለ ሞዓብ ትዕቢት እጅግ ስለ መታበዩ፥ ስለ ኵራቱና ስለ ትዕቢቱ ስለ ቍጣውም ሰምተናል፤ ትምሕክቱ ከንቱ ነው።

7፤ ስለዚህ ሞዓብ ስለ ሞዓብ ዋይ ይላል፤ ሁሉም ዋይ ይላል፤ ስለ ቂርሐራሴት መሠራት በጥልቅ ኀዘን ታለቅሳላችሁ።

8፤ የሐሴቦን እርሻዎችና የሴባማ ወይን ግንዶች አዝነዋል። የአሕዛብ አለቆች የሰባበሩአቸው ቅርንጫፎች እስከ ኢያዜር ደርሰው ወደ ምድረ በዳ ወጥተው ነበር፤ ቍጥቋጦቹም ተዘርግተው ባሕርን ተሻግረው ነበር።

9፤ ስለዚህ በኢያዜር ልቅሶ ስለ ሴባማ ወይን ግንድ አለቅሳለሁ፤ ሐሴቦንና ኤልያሊ ሆይ፥ በዛፍሽ ፍሬና በወይንሽ መከር የጦር ጩኸት ወድቆአልና በእንባዬ አረካሻለሁ።

10፤ ደስታና ሐሤትም ከፍሬያማው እርሻ ተወስዶአል፥ በወይኑም ቦታዎች ዝማሬና እልልታ የለም፤ በመጥመቂያም ወይን የሚረግጥ የለም፤ የረጋጮቹን እልልታ አጥፍቻለሁ።

11፤ ስለዚህ ልቤ ስለ ሞዓብ አንጀቴም ስለ ቂርሔሬስ እንደ መሰንቆ ትጮኻለች።

12፤ ሞዓብም መጥቶ በኮረብታ መስገጃ ላይ በደከመና ለጸሎት ወደ መቅደሱ በገባ ጊዜ አያሸንፍም

13፤ እግዚአብሔር በሞዓብ ላይ በድሮ ዘመን የተናገረው ነገር ይህ ነው።

14፤ አሁን ግን እግዚአብሔር። በሦስት ዓመት ውስጥ እንደ ምንደኛ ዓመት የሞዓብ ክብርና የሕዝቡ ሁሉ ብዛት ይዋረዳል፥ ቅሬታውም እጅግ ያነሰና የተጠቃ ይሆናል ይላል።