ምዕራፍ 2።

1፤ የአሞጽ ልጅ ኢሳይያስ ስለ ይሁዳና ስለ ኢየሩሳሌም ያየው ቃል።

2፤ በዘመኑም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ቤት ተራራ በተራሮች ራስ ላይ ጸንቶ ይቆማል፥ ከኮረብቶችም በላይ ከፍ ከፍ ይላል፥ አሕዛብም ሁሉ ወደ እርሱ ይሰበሰባሉ።

3፤ ሕግ ከጽዮን የእግዚአብሔርም ቃል ከኢየሩሳሌም ይወጣልና ብዙዎች አሕዛብ ሄደው። ኑ፥ ወደ እግዚአብሔር ተራራ፥ ወደ ያዕቆብ አምላክ ቤት እንውጣ፤ እርሱም መንገዱን ያስተምረናል፥ በጎዳናውም እንሄዳለን ይላሉ።

4፤ በአሕዛብም መካከል ይፈርዳል፥ በብዙ አሕዛብም ላይ ይበይናል፤ ሰይፋቸውንም ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፥ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።

5፤ እናንተ የያዕቆብ ቤት ሆይ፥ ኑ፥ በእግዚአብሔር ብርሃን እንሂድ።

6፤ ሕዝብህን የያዕቆብን ቤት ትተሃልና፤ ይኸውም የምሥራቅን ሰዎች አመል ስለ ተሞሉ፥ እንደ ፍልስጥኤማውያንም ምዋርተኞች ስለ ሆኑ፥ ከባዕድ ልጆችም ጋር ስለ ተባበሩ ነው።

7፤ ምድራቸው በብርና በወርቅ ተሞልታለች፥ ለመዛግብቶቻቸውም ፍጻሜ የለውም፤ ምድራቸውም ደግሞ በፈረሶች ተሞልታለች፥ ለሠረገሎቻቸውም ፍጻሜ የለውም።

8፤ ምድራቸው ደግሞ በጣዖታት ተሞልታለች፤ ጣቶቻቸውም ላደረጉት ለእጃቸው ሥራ ይሰግዳሉ።

9፤ ታናሹም ሰው ዝቅ ብሎአል፥ ጨዋውም ተዋርዶአል፤ ኃጢአታቸውንም ይቅር አትበላቸው።

10፤ ከእግዚአብሔር ማስደንገጥና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻ ግባ፥ በመሬትም ውስጥ ተሸሸግ።

11፤ ከፍ ያለችውም የሰው ዓይን ትዋረዳለች፥ የሰዎችም ኵራት ትወድቃለች፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻውን ከፍ ከፍ ይላል።

12፤ የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር ቀን በትዕቢተኛውና በኵራተኛው ሁሉ ላይ ከፍ ባለውም ላይ ይሆናል፥ እርሱም ይዋረዳል፤

13፤ ደግሞም በረጅሙ ከፍ ባለው በሊባኖስ ዝግባ ሁሉ ላይ፥ በባሳንም ዛፍ ሁሉ ላይ፥

14፤ በረጅሙም ተራራ ሁሉ ላይ፥ ከፍ ባለውም ኮረብታ ሁሉ ላይ፥

15፤ በረጅሙም ግንብ ሁሉ ላይ፥ በተመሸገውም ቅጥር ሁሉ ላይ፥

16፤ በተርሴስም መርከብ ሁሉ ላይ፥ በሚያማምሩ ጣዖታትም ሁሉ ላይ ይሆናል።

17፤ ሰውም ሁሉ ይዋረዳል፥ የሰውም ኵራት ይወድቃል፥ በዚያም ቀን እግዚአብሔር ብቻ ከፍ ከፍ ይላል።

18፤ ጣዖቶቻቸውም ሁሉ ፈጽመው ይጠፋሉ።

19፤ እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ሰዎች ከማስደንገጡና ከግርማው ክብሩ የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ምድር ንቃቃት ውስጥ ይገባሉ።

20፤ በዚያን ቀን ሰው ይሰግድላቸው ዘንድ ያበጁአቸውን የብሩንና የወርቁን ጣዖቶቹን ለፍልፈልና ለሌሊት ወፍ ይጥላል።

21፤ እግዚአብሔርም ምድርን ያናውጥ ዘንድ በተነሣ ጊዜ ከማስደንገጡና ከግርማው ክብር የተነሣ ወደ ድንጋይ ዋሻና ወደ ተሰነጠቁ ዓለቶች ውስጥ ይገባሉ።

22፤ እስትንፋሱ በአፍንጫው ውስጥ ያለበትን ሰው ተዉት፤ እርሱ ስለ ምን ይቈጠራል?