ምዕራፍ 2።

1፤ የእስራኤልም ልጆች ቍጥር እንደማይሰፈርና እንደማይቈጠር እንደ ባሕር አሸዋ ይሆናል፤ እንዲህም ይሆናል፤ እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም ተብሎ በተነገረበት በዚያ ስፍራ የሕያው አምላክ ልጆች ይባላሉ።

2፤ የይሁዳ ልጆችና የእስራኤል ልጆች በአንድነት ይሰበሰባሉ፥ ለእነርሱም አንድ አለቃ ይሾማሉ፥ ከምድሪቱም ይወጣሉ፤ የኢይዝራኤል ቀን ታላቅ ይሆናልና።

3፤ ወንድሞቻችሁን። ዓሚ፥ እኅቶቻችሁንም። ሩሃማ በሉአቸው።

4፤ እናታችሁ ሚስቴ አይደለችምና፥ እኔም ባልዋ አይደለሁምና ተምዋገቱ፤ ከእናታችሁ ጋር ተምዋገቱ። ግልሙትናዋን ከፊትዋ፥ ምንዝርናዋንም ከጡቶችዋ መካከል ታስወግድ፤

5፤ ዕራቁትዋን እንዳልገፍፋት፥ እንደ ተወለደችበትም ቀን እንዳላደርጋት፥ እንደ ምድረ በዳና እንደ ደረቅ ምድር እንዳላደርጋት፥ በጥማትም እንዳልገድላት፤

6፤ የግልሙትናዋ ልጆች ናቸውና ልጆችዋን አልምርም።

7፤ እናታቸው አመንዝራለች፤ የፀነሰቻቸውም። እንጀራዬንና ውኃዬን፥ ጥጤንና የተልባ እግሬን፥ ዘይቴንና መጠጤን ከሚሰጡኝ ከውሽሞቼ በኋላ እሄዳለሁ ብላ አስነወረቻቸው።

8፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ መንገድሽን በእሾህ እዘጋለሁ፥ መንገድዋንም እንዳታገኝ ቅጥርን እቀጥርባታለሁ።

9፤ ውሽሞችዋንም ትከተላለች፥ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ ትፈልጋቸውማለች፥ ነገር ግን አታገኛቸውም፤ እርስዋም። ከዛሬ ይልቅ የዚያን ጊዜ ይሻለኝ ነበርና ተመልሼ ወደ ቀደመው ባሌ እሄዳለሁ ትላለች።

10፤ እርስዋም እህልንና ወይንን ጠጅ ዘይትንም የሰጠኋት፥ ለበኣልም የተሠራውን ብርና ወርቅ ያበዛሁላት እኔ እንደ ሆንሁ አላወቀችም።

11፤ ስለዚህ እህሌን በጊዜዋ፥ ወይን ጠጄንም በወረትዋ እወስዳለሁ፥ ዕራቁትነትዋንም እንዳትሸፍን ጥጤንና የተልባ እግሬን እገፍፋታለሁ።

12፤ አሁንም ውሽሞችዋ እያዩ ነውርዋን እገልጣለሁ፤ ከእጄም ማንም አያድናትም።

13፤ ደስታዋንም ሁሉ፥ በዓላቶችዋንም፥ መባቻዎችዋንም፥ ሰንበቶችዋንም፥ የተቀደሱትንም ጉባኤዎችን ሁሉ አስቀራለሁ።

14፤ እርስዋም። ውሽሞቼ የሰጡኝ ዋጋዬ ይህ ነው ያለችውን ወይንዋንና በለስዋን አጠፋለሁ፤ ዱርም አደርገዋለሁ፥ የምድረ በዳም አራዊት ይበሉታል።

15፤ እኔን ረስታ ውሽሞችዋን እየተከተለች፥ በጕትቾችዋና በጌጥዋም እያጌጠች ለበኣሊም ያጠነችበትን ወራት እበቀልባታለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር።

16፤ ስለዚህ፥ እነሆ፥ አባብላታለሁ፥ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ፥ ለልብዋም እናገራለሁ።

17፤ ከዚያም የወይን ቦታዋን፥ የተስፋ በርም እንዲሆንላት የአኮርን ሸለቆ እሰጣታለሁ፤ በዚያም ከግብጽ ምድር እንደ ወጣችበት ቀን እንደ ሕፃንነትዋ ወራት ትዘምራለች።

18፤ በዚያ ቀን ባሌ ብለሽ ትጠሪኛለሽ እንጂ ዳግመኛ በኣሌ ብለሽ አትጠሪኝም፥ ይላል እግዚአብሔር፤

19፤ የበኣሊምን ስም ከአፍዋ አስወግደዋለሁና፥ በስማቸውም እንግዲህ አይታሰቡምና።

20፤ በዚያም ቀን ከምድር አራዊትና ከሰማይ ወፎች ከመሬትም ተንቀሳቃሾች ጋር ቃል ኪዳን አደርግላቸዋለሁ፤ ቀስትንና ሰይፍን ሰልፍንም ከምድሩ እሰብራለሁ፥ ተከልለውም እንዲኖሩ አስተኛቸዋለሁ።

21፤ ለዘላለምም ለእኔ እንድትሆኚ አጭሻለሁ፤ በጽድቅና በፍርድ በምሕረትና በርኅራኄ አጭሻለሁ።

22፤ ለእኔም እንድትሆኚ በመታመን አጭሻለሁ፤ አንቺም እግዚአብሔርን ታውቂአለሽ።

23፤ በዚያንም ቀን እመልሳለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ ለሰማይ እመልሳለሁ፥ ሰማይም ለምድር ይመልሳል፤

24፤ ምድርም ለእህልና ለወይን ጠጅ ለዘይትም ትመልሳለች፤ እነርሱም ለኢይዝራኤል ይመልሳሉ።

25፤ በምድርም ላይ ለእኔ እዘራታለሁ፤ ምሕረትም የሌላትን እምራለሁ፥ ሕዝቤም ያልሆነውን። አንተ ሕዝቤ ነህ እለዋለሁ፤ እርሱም። አንተ አምላኬ ነህ ይለኛል።