ምዕራፍ 3

1 የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች ሆይ፥ በዓይናችሁ ፊት ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ ተሰቀለ ሆኖ ተሥሎ ነበር፤ ለእውነት እንዳትታዘዙ አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው?

2 ይህን ብቻ ከእናንተ እንድማር እወዳለሁ፤ በሕግ ሥራ ወይም ከእምነት ጋር በሆነ መስማት መንፈስን ተቀበላችሁን?

3 እንዲህን የማታስተውሉ ናችሁ? በመንፈስ ጀምራችሁ አሁን በሥጋ ትፈጽማላችሁን?

4 በውኑ ከንቱ እንደ ሆነስ እንደዚህ ያለ መከራ በከንቱ ተቀበላችሁን?

5 እንግዲህ መንፈስን የሚሰጣችሁ በእናንተም ዘንድ ተአምራት የሚያደርግ፥ በሕግ ሥራ ነውን ወይስ ከእምነት ጋር በሆነ መስማት ነው?

6 እንዲሁ አብርሃም በእግዚአብሔር አመነና ጽድቅ ሆኖ ተቆጠረለት።

7 እንኪያስ ከእምነት የሆኑት እነዚህ የአብርሃም ልጆች እንደ ሆኑ እወቁ።

8 መጽሐፍም እግዚአብሔር አሕዛብን በእምነት እንዲያጸድቅ አስቀድሞ አይቶ። በአንተ አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ ብሎ ወንጌልን ለአብርሃም አስቀድሞ ሰበከ።

9 እንደዚህ ከእምነት የሆኑት ካመነው ከአብርሃም ጋር ይባረካሉ።

10 ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና።

11 ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው።

12 ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን። የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል።

13 በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤

14 የመንፈስን ተስፋ በእምነት እንድንቀበል፥ የአብርሃም በረከት ወደ አሕዛብ በኢየሱስ ክርስቶስ ይደርስላቸው ዘንድ።

15 ወንድሞች ሆይ፥ እንደ ሰው ልማድ እላለሁ። የሰው ስንኳ ቢሆን እርግጠኛውን ኪዳን ማንም አይንቅም ወይም አይጨምርበትም።

16 ለአብርሃምና ለዘሩም የተስፋው ቃል ተነገረ። ስለ ብዙዎች እንደሚነገር። ለዘሮቹም አይልም፤ ስለ አንድ እንደሚነገር ግን። ለዘርህም ይላል፥ እርሱም ክርስቶስ።

17 ይህንም እላለሁ፤ ከአራት መቶ ሠላሳ ዓመት በኋላ የተሰጠው ሕግ አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተረጋገጠውን ኪዳን የተስፋውን ቃል እስኪሽር ድረስ አያፈርስም።

18 ርስቱ በሕግ ቢሆንስ እንግዲያስ በተስፋ ቃል አይሆንም፤ በተስፋ ቃል ግን እግዚአብሔር ለአብርሃም ሰጥቶአል።

19 እንግዲህ ሕግ ምንድር ነው? ተስፋው የተሰጠው ዘር እስኪመጣ ድረስ በመካከለኛ እጅ በመላእክት በኩል ስለ ሕግ መተላለፍ ተጨመረ።

20 መካከለኛውም ለአንድ ብቻ አይደለም እግዚአብሔር ግን አንድ ነው።

21 እንግዲህ ሕግ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል የሚቃወም ነውን? አይደለም። ሕያው ሊያደርግ የሚቻለው ሕግ ተሰጥቶ ቢሆንስ በእውነት ጽድቅ ከሕግ በሆነ ነበር፤

22 ነገር ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ከማመን የሆነው የተስፋ ቃል ለሚያምኑ ይሰጥ ዘንድ መጽሐፍ ከኃጢአት በታች ሁሉን ዘግቶታል።

23 እምነትም ሳይመጣ ሊገለጥ ላለው እምነት ተዘግተን ከሕግ በታች እንጠበቅ ነበር።

24 እንደዚህ በእምነት እንጸድቅ ዘንድ ሕግ ወደ ክርስቶስ የሚያመጣ ሞግዚታችን ሆኖአል፤

25 እምነት ግን መጥቶአልና ከእንግዲህ ወዲህ ከሞግዚት በታች አይደለንም።

26 በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤

27 ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።

28 አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና።

29 እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።