ምዕራፍ 6።

1፤ በዚያ ጊዜም ንጉሡ ዳርዮስ መዛግብት ባሉበት በባቢሎን ቤተ መጻሕፍት እንዲመረመር አዘዘ።

2፤ በሜዶን አውራጃ ባለው አሕምታ በሚባል ከተማ በንጉሡ ቤት ውስጥ አንድ ጥቅልል ተገኘ፥ በውስጡም ይህ ነገር ለመታሰቢያ ተጽፎ ነበር።

3፤ በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ እንዲህ ብሎ አዘዘ፤ በኢየሩሳሌም ያለው የእግዚአብሔር ቤት፥ መሥዋዕት የሚቀርብበት ቦታ፥ ይህ ቤት ይሠራ፥ በጽኑም ይመሥረት፤ ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን።

4፤ በሦስት ተራ ታላላቅ ድንጋይ፥ በአንድ ተራ እንጨት ይደረግ፤ ውጪውም ከንጉሡ ቤት ይሰጥ።

5፤ ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው መቅደስ ወስዶ ወደ ባቢሎን ያመጣው የእግዚአብሔር ቤት የወርቅና የብር ዕቃ ይመለስ፤ በኢየሩሳሌምም ወዳለው መቅደስ ወደ ስፍራው ይወሰድ፥ በእግዚአብሔር ቤት ይኑር።

6፤ አሁንም አንተ በወንዝ ማዶ ያለኸው የአገሩ ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ በወንዝ ማዶም ያሉ ተባባሪዎቻችሁ አፈርስካውያን፥ ከዚያ ራቁ፤

7፤ ይህም የእግዚአብሔር ቤት ይሠራ ዘንድ ተዉ፤ የአይሁድም አለቃና የአይሁድም ሽማግሌዎች ይህን የእግዚአብሔርን ቤት በስፍራው ይሠሩ ዘንድ ተዉአቸው።

8፤ ይህን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ ለአይሁድ ሽማግሌዎች የምታደርጉትን፥ በወንዝ ማዶ ካለው አገር ከሚመጣው ግብር ከንጉሡ ገንዘብ ለእነዚህ ሰዎች ወጪውን በትጋት እንድትሰጡአቸው ሥራም እንዳታስፈቱአቸው አዝዣለሁ።

9፤ ለሰማይ አምላክ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚያስፈልገውን፥ ወይፈኖችና አውራ በጎች ጠቦቶችም፥ በኢየሩሳሌምም እንዳሉ እንደ ካህናቱ ቃል ስንዴና ጨው የወይን ጠጅና ዘይት ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ስጡአቸው።

10፤ ይኸውም ለሰማይ አምላክ ጣፋጭ ሽቱ የሆነውን መሥዋዕት ያቀረቡ ዘንድ ለንጉሡና ለልጆቹም ዕድሜ ይጸልዩ ዘንድ ነው።

11፤ ይህንም ትእዛዝ የሚለውጥ ሁሉ፥ ምሰሶው ከቤቱ ተነቅሎ እርሱ ይሰቀልበት፤ ቤቱም የጉድፍ መጣያ ይደረግ ብዬ አዝዣለሁ።

12፤ ስሙንም በዚያ ያኖረው አምላክ ይህን ይለውጡ ዘንድ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤት ያፈርሱት ዘንድ እጃቸውን የሚዘረጉትን ነገሥታትና አሕዛብ ሁሉ ያጥፋ። እኔ ዳርዮስ ይህን አዝዣለሁ፤ በትጋት ይፈጸም።

13፤ ንጉሡም ዳርዮስ እንደ ላከው ቃል፥ በዚያን ጊዜ በወንዝ ማዶ ያለ ገዥ ተንትናይ ደግሞ ሰተርቡዝናይ ተባባሪዎቻቸውም እንዲሁ ተግተው አደረጉ።

14፤ የአይሁድም ሽማግሌዎች በነቢዩ በሐጌና በአዶ ልጅ በዘካርያስ ትንቢት ሠሩ ተከናወነላቸውም። እንደ እስራኤልም አምላክ ትእዛዝ፥ እንደ ፋርስም ነገሥታት እንደ ቂሮስና እንደ ዳርዮስ እንደ አርጤክስስም ትእዛዝ ሠርተው ፈጸሙ።

15፤ ይህም ቤት በንጉሡ በዳርዮስ መንግሥት በስድስተኛው ዓመት አዳር በሚባል ወር በሦስተኛው ቀን ተፈጸመ።

16፤ የእስራኤልም ልጆች፥ ካህናትና ሌዋውያን የቀሩትም ምርኮኞች፥ የዚህን የእግዚአብሔርን ቤት ቅዳሴ በደስታ አደረጉ።

17፤ በዚህም በእግዚአብሔር ቤት ቅዳሴ መቶ ወይፈኖችና ሁለት መቶ አውራ በጎች አራት መቶም ጠቦቶች አቀረቡ ፤ ስለ ኃጢአትም መሥዋዕት እንደ እስራኤል ነገዶች ቍጥር ለእስራኤል ሁሉ አሥራ ሁለት አውራ ፍየሎች አቀረቡ።

18፤ በሙሴም መጽሐፍ እንደ ተጻፈው በኢየሩሳሌም ባለው በእግዚአብሔር አገልግሎት ላይ ካህናቱን በየማዕርጋቸው ሌዋውያኑም በየክፍላቸው አቆሙ።

19፤ ምርኮኞቹም በመጀመሪያው ወር በአሥራ አራተኛው ቀን ፋሲካውን አደረጉ።

20፤ ካህናቱና ሌዋውያኑም አንድ ሆነው ነጽተው ነበር፤ ሁሉም ንጹሐን ነበሩ፤ ለምርኮኞቹም ሁሉ፥ ለወንድሞቻቸውም ለካህናቱ፥ ለራሳቸውም ፋሲካውን አረዱ።

21፤ ከምርኮም ተመልሰው የመጡት የእስራኤል ልጆች፥ የእስራኤልንም አምላክ እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ ራሳቸውን ከምድር አሕዛብ ርኵሰት ለይተው ወደ እነርሱ መጥተው የነበሩት ሁሉ በሉ፤

22፤ እግዚአብሔር ደስ አሰኝቶአቸዋልና፥ የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት እጃቸውን ያጸና ዘንድ የአሦርን ንጉሥ ልብ ወደ እነርሱ መልሶአልና የቂጣውን በዓል ሰባት ቀን በደስታ አደረጉ።