ምዕራፍ 42።

1፤ በውጭም አደባባይ በሰሜኑ መንገድ አወጣኝ፥ በልዩውም ስፍራ አንጻርና በሰሜን በኩል ባለው ግቢ ፊት ለፊት ወዳለው ዕቃ ቤት አገባኝ።

2፤ መቶ ክንድ በሆነው ርዝመት ፊት በሰሜን በኩል መዝጊያ ነበረ ወርዱም አምሳ ክንድ ነበረ።

3፤ በውስጠኛውም አደባባይ በሀያው ክንድ አንጻር በውጭውም አደባባይ በወለሉ አንጻር በሦስት ደርብ በትይዩ የተሠራ መተላለፊያ ነበረ።

4፤ በዕቃ ቤቶቹም ፊት በስተ ውስጥ ወርዱ አሥር ክንድ ርዝመቱ መቶ ክንድ የሆነ መንገድ ነበረ፤ መዝጊያዎቻቸውም ወደ ሰሜን ይመለከቱ ነበር።

5፤ መተላለፊያውም አሳጥሮአቸዋልና ላይኞቹ ዕቃ ቤቶች ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ አጫጭር ነበሩ።

6፤ በሦስትም ደርብ ተሠርተው ነበርና፥ በአደባባዩም እንዳሉት አዕማድ፥ አዕማድ አልነበሩላቸውምና ስለዚህ ላይኞቹ ከመካከለኞቹና ከታችኞቹ ይልቅ ጠባብ ነበሩ።

7፤ በውጭ በዕቃ ቤቶቹ አጠገብ ያለው፥ ወደ ውጭው አደባባይ የሚመለከተው ቅጥር፥ በዕቃ ቤቶች ትይዩ የሆነ፥ ርዝመቱ አምሳ ክንድ ነበረ።

8፤ በመቅደሱ ፊት የነበሩት ዕቃ ቤቶች ርዝመታቸው መቶ ክንድ ሲሆን በውጭው አደባባይ በኩል የነበሩት ዕቃ ቤቶች ርዝመታቸው አምሳ ክንድ ነበረና።

9፤ ከእነዚህም ዕቃ ቤቶች በታች በስተ ምሥራቅ በኩል፥ ሰው ከውጭው አደባባይ የሚገባበት መግቢያ ነበረ። ይህም በቅጥሩ ራስ አጠገብ ነበረ።

10፤ በደቡብም በኩል በልዩው ስፍራና በግቢው አንጻር ዕቃ ቤቶች ነበሩ።

11፤ በስተ ፊታቸውም የነበረ መንገድ በሰሜን በኩል እንደ ነበረው እንደ ዕቃ ቤቶቹ መንገድ ምስያ ነበረ። ርዝመታቸውም ወርዳቸውም መውጫቸውም ሥርዓታቸውም መዝጊያዎቻቸውም በዚያው ልክ ነበረ።

12፤ በደቡብም በኩል ካሉት ዕቃ ቤቶች በታች በምሥራቅ በኩል በቅጥሩ ራስ አጠገብ መግቢያ ነበረ።

13፤ እንዲህም አለኝ። በልዩ ስፍራ አንጻር በሰሜንና በደቡብ በኩል ያሉ ዕቃ ቤቶች፥ እነርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚቀርቡ ካህናት ከሁሉ ይልቅ የተቀደሰውን ምግብ የሚበሉባቸው ቤቶች ናቸው። ስፍራው ቅዱስ ነውና በዚያ የተቀደሰውን ነገር የእህሉን ቍርባን የኃጢአቱንና የበደሉን መሥዋዕት ያኖራሉ።

14፤ ካህናቱም በገቡ ጊዜ ከመቅደሱ በውጭው አደባባይ አይወጡም፤ የሚያገለግሉበትን ልብሳቸውን ግን ቅዱስ ነውና በዚያ ያኖሩታል፥ ሌላም ልብስ ለብሰው ወደ ሕዝብ ይወጣሉ።

15፤ ውስጠኛውንም ቤት ለክቶ በፈጸመ ጊዜ ወደ ምሥራቅ በሚመለከት በር መንገድ አወጣኝ እርሱንም በዙሪያው ለካው።

16፤ የምሥራቁን ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።

17፤ ዞረም፥ የሰሜኑንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።

18፤ ዞረም፥ የደቡቡንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።

19፤ ዞረም፥ የምዕራቡንም ወገን በመለኪያ ዘንግ አምስት መቶ ክንድ አድርጎ ለካ።

20፤ በአራቱ ወገን ለካው። የተቀደሰውንና ያልተቀደሰውን ይለይ ዘንድ ርዝመቱ አምስት መቶ ክንድ ወርዱም አምስት መቶ ክንድ የሆነ ቅጥር በዙሪያው ነበረ።