ምዕራፍ 24።

1፤ በዘጠነኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

2፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ የዚህን ቀን፥ የዛሬን ቀን ስም ጻፍ፤ በዚህ ቀን የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ቀረበ።

3፤ ለዓመፀኛውም ቤት ምሳሌን ተናገር እንዲህም በላቸው። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ጣድ፥ ምንቸቲቱን ጣድ፥ ውኃም ጨምርባት።

4፤ ቍራጭዋንም፥ መልካሙን ቍራጭ ሁሉ፥ ጭኑንና ወርቹን በእርስዋ ውስጥ ሰብስብ፥ የተመረጡትንም አጥንቶች ሙላባት።

5፤ ከመንጋው የተመረጠውን ውሰድ፥ አጥንቶቹም እንዲበስሉ እንጨት በበታችዋ ማግድ፤ አጥንቶቹም በውስጥዋ ይቀቀሉ።

6፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ዝገትዋ ላለባት ዝገትዋም ከእርስዋ ላልወጣ ምንቸት፥ ለደም ከተማ ወዮላት! ቍራጭ ቍራጩን አውጣ፤ ዕጣ አልወደቀባትም።

7፤ ደምዋ በውስጥዋ አለ። በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረገችው እንጂ በአፈር ይከደን ዘንድ በመሬት ላይ አላፈሰሰችውም፤

8፤ መዓቴን አወጣ ዘንድ፥ በቀሌንም እበቀል ዘንድ፥ ደምዋ እንዳይከደን በተራቈተ ድንጋይ ላይ አደረግሁ።

9፤ ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። ለደም ከተማ ወዮላት! እኔ ደግሞ ማገዶዋን ታላቅ አደርገዋለሁ።

10፤ እንጨቱን አብዛ፤ እሳቱን አንድድ፤ ሥጋውን ቀቅል፤ መረቁን አጣፍጠው፤ አጥንቶቹ ይቃጠሉ።

11፤ ትሞቅም ዘንድ ናስዋም ትግል ዘንድ ርኵሰትዋም በውስጥዋ ይቀልጥ ዘንድ ዝገትዋም ይጠፋ ዘንድ ባዶዋን በፍም ላይ አድርጋት።

12፤ በከንቱ ደከመች፤ ሆኖም ዝገትዋ በእሳት ስንኳ አልለቀቀም።

13፤ በርኵሰትሽ ሴሰኝነት አለ፤ አነጻሁሽ አልነጻሽምና መዓቴን በላይሽ እስክጨርስ ድረስ እንግዲህ ከርኵሰትሽ አትነጺም።

14፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ ይመጣል፥ እኔም አደርገዋለሁ፤ አልመለስም፥ አልራራም፥ አልጸጸትም፤ እንደ መንገድሽና እንደ ሥራሽ ይፈርዱብሻል፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

15፤ የእግዚአብሔርም ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

16፤ የሰው ልጅ ሆይ፥ እነሆ፥ የዓይንህን አምሮት በመቅሠፍት እወስድብሃለሁ፤ አንተም ወይ አትበል አታልቅስም እንባህንም አታፍስስ።

17፤ በቀስታ ተክዝ፤ ለምዋቾችም አታልቅስ፥ መጠምጠሚያህን በራስህ ላይ አድርግ፥ ጫማህንም በእግርህ አጥልቅ፥ ከንፈሮችህንም አትሸፍን የሰዎችንም እንጀራ አትብላ።

18፤ እኔም በማለዳ ለሕዝቡ ተናገርሁ፥ ወደ ማታም ሚስቴ ሞተች፤ በነጋውም እንደ ታዘዝሁ አደረግሁ።

19፤ ሕዝቡም። ይህ የምታደርገው ነገር ለእኛ ምን እንደ ሆነ አትነግረንምን? አሉኝ።

20፤ እኔም እንዲህ አልኋቸው። የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ።

21፤ ለእስራኤል ቤት ተናገር እንዲህም በል። ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ የኃይላችሁን ትምክሕት፥ የዓይናችሁን አምሮት፥ የነፍሳችሁን ምኞት መቅደሴን አረክሳለሁ፤ ያስቀራችኋቸውም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችሁ በሰይፍ ይወድቃሉ።

22፤ እኔም እንዳደረግሁ እናንተ ታደርጋላችሁ፤ ከንፈራችሁን አትሸፍኑም የሰዎችንም እንጀራ አትበሉም።

23፤ መጠምጠሚያችሁም በራሳችሁ ጫማችሁም በእግራችሁ ይሆናል፤ ዋይ አትሉም አታለቅሱምም፤ በኃጢአታችሁም ትሰለስላላችሁ፥ እርስ በርሳችሁም ታንጐራጕራላችሁ።

24፤ ሕዝቅኤልም ምልክት ይሆናችኋል፤ እርሱ እንዳደረገ ሁሉ እናንተ ታደርጋላችሁ፤ ይህም በመጣ ጊዜ እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቃላችሁ።

25፤ አንተም የሰው ልጅ ሆይ፥ ኃይላቸውን፥ የተመኩበትንም ደስታ፥ የዓይናቸውን አምሮት፥ የነፍሳቸውንም ምኞት፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውን በወሰድሁባቸው ቀን፥

26፤ በዚያ ቀን ያመለጠው ይህን ነገር በጆሮህ ያሰማ ዘንድ ወደ አንተ ይመጣል።

27፤ በዚያ ቀን አፍህ ላመለጠው ይከፈታል፥ አንተም ትናገራለህ ከዚያ ወዲያም ዲዳ አትሆንም፤ ምልክትም ትሆናቸዋለህ፥ እኔም እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ያውቃሉ።