ምዕራፍ 30።

1፤ የዕጣን መሠዊያውን ሥራ፤ ከግራር እንጨት አድርገው።

2፤ ርዝመቱ አንድ ክንድ፥ ስፋቱም አንድ ክንድ፥ አራት ማዕዘን ይሁን፤ ከፍታውም ሁለት ክንድ ይሆናል፤ ቀንዶቹም ከእርሱ ጋር በአንድነት የተሠሩ ይሁኑ።

3፤ ላይኛውንና የግድግዳውንም ዙሪያ ቀንዶቹንም በጥሩ ወርቅ ትለብጠዋለህ፤ በዙሪያውም የወርቅ ክፈፍ ታደርግለታለህ።

4፤ ከክፈፉም በታች ሁለት የወርቅ ቀለበቶች አድርግለት። በዚህና በዚያ በሁለቱ ጎን ታደርጋቸዋለህ፤ ለመሸከምም የመሎጊያዎች ስፍራ ይሁኑ።

5፤ መሎጊያዎቹንም ከግራር እንጨት አድርግ፥ በወርቅም ለብጣቸው።

6፤ በምስክሩ ታቦት አጠገብም ካለው መጋረጃ በፊት ታኖረዋለህ ይህንም አንተን በምገናኝበት ከምስክሩ በላይ ባለው በስርየት መክደኛ ፊት ታኖረዋለህ።

7፤ አሮንም የጣፋጭ ሽቱ እጣን ይጠንበት፤ በማለዳ በማለዳ መብራቶቹን ሲያዘጋጅ ይጠነው።

8፤ ይህን በእግዚአብሔር ፊት ለልጅ ልጃችሁ የዘወትር ዕጣን ይሆን ዘንድ አሮን በማታ ጊዜ መብራቶቹን ሲያበራ ያጥነዋል።

9፤ ሌላም ዕጣን፥ የሚቃጠለውንም መስዋዕት፥ የእህሉንም ቍርባን አታቀርብበትም፤ የመጠጥም ቍርባን አታፈስስበትም።

10፤ አሮንም በአመት አንድ ጊዜ በቀንዶቹ ላይ ማስተስረያ ያደርጋል፤ በአመት አንድ ጊዜ ለልጅ ልጃችሁ ማስተስረያ በሚሆን በኃጢአት መሥዋዕት ደም ማስተስረያ ያደርግበታል። ለእግዚአብሔር ቅድስተ ቅዱሳን ናት።

11፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

12፤ አንተ የእስራኤልን ልጆች ቍጥር ተቀብለህ፥ በቈጠርሃቸው ጊዜ መቅሰፍት እንዳይሆንባቸው፥ በቈጠርሃቸው ጊዜ ከእነርሱ ሰው ሁሉ እንደ ቍጥራቸው መጠን የነፍሱን ቤዛ ለእግዚአብሔር ይስጥ።

13፤ አልፎ የሚቈጠር ሁሉ ግማሽ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን ይሰጣል፤ የሰቅል ግማሽ ለእግዚአብሔር ያነሣል።

14፤ ሰቅሉ ሀያ ኦቦሊ ነው። አልፎ የተቈጠረ ሁሉ፥ ከሀያ ዓመት ጀምሮ ከዚያም ከፍ ያለ፥ የእግዚአብሔርን ስጦታ ይሰጣል።

15፤ ለነፍሳችሁ ማስተስረያ የእግዚአብሔርን ስጦታ ስትሰጡ ባለ ጠጋው ከሰቅል ግማሽ አይጨምር፥ ድሀውም አያጕድል።

16፤ የማስተስረያውንም ገንዘብ ከእስራኤል ልጆች ወስደህ ለመገናኛው ድንኳን ማገልገያ ታደርገዋለህ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ለነፍሳችሁ ቤዛ እንዲሆን ለእስራኤል ልጆች መታሰቢያ ይሁን።

17፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

18፤ የመታጠቢያ ሰንና መቀመጫውን ከናስ ሥራ፤ በመገናኛው ድንኳንና በመሠዊያው መካከል እርሱን አድርገህ ውኃን ትጨምርበታለህ።

19፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡበታል።

20፤ ወደ መገናኛው ድንኳን በገቡ ጊዜ፥ ለእግዚአብሔርም የእሳት መስዋዕት ያቃጥሉ ዘንድ ወደ መሠዊያው ሊያገለግሉ በቀረቡ ጊዜ፥ እንዳይሞቱ ይታጠቡበታል።

21፤ እንዳይሞቱም እጆቻቸውንና እግሮቻቸውን ይታጠቡ፤ ይህም ለእርሱ ከእርሱም በኋላ ለዘሩ የዘላለም ሥርዓት ይሆንላቸዋል።

22፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

23፤ አንተም ክቡሩን ሽቱ ውሰድ፤ የተመረጠ ከርቤ አምስት መቶ ሰቅል፥ ግማሽም ጣፋጭ ቀረፋ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥ የጠጅ ሣርም እንዲሁ ሁለት መቶ አምሳ ሰቅል፥

24፤ ብርጕድም አምስት መቶ ሰቅል እንደ መቅደሱ ሰቅል ሚዛን፥ የወይራ ዘይትም አንድ የኢን መስፈሪያ ትወስዳለህ።

25፤ በቀማሚም ብልሃት እንደ ተሠራ ቅመም፥ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ታደርገዋለህ፤ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሆናል።

26፤ የመገናኛውንም ድንኳን፥ የምስክሩንም ታቦት፥

27፤ ገበታውንም ዕቃውንም ሁሉ፥ መቅረዙንም ዕቃውንም፥ የዕጣን መሠዊያውንም፥

28፤ ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን መሠዊያና ዕቃውንም ሁሉ፥ የመታጠቢያውን ሰንና መቀመጫውንም ትቀባበታለህ።

29፤ ሁሉንም ትቀድሳቸዋለህ፥ ቅድስተ ቅዱሳንም ይሆናሉ፤ የሚነካቸውም ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።

30፤ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ቅባቸው፥ ቀድሳቸውም።

31፤ አንተም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ተናገር። ይህ ለልጅ ልጃችሁ የተቀደሰ የቅብዓት ዘይት ይሁንልኝ።

32፤ በሰው ሥጋ ላይ አይፍሰስ፤ እንደ እርሱም የተሰራ ሌላ ቅብዓት አታድርጉ፤ ቅዱስ ነው፥ ለእናንተም ቅዱስ ይሁን።

33፤ እንደ እርሱ ያለውን የሚያደርግ ሰው፥ በሌላም ሰው ላይ የሚያፈስሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።

34፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። ጣፋጭ ሽቱ ውሰድ፤ የሚንጠባጠብ ሙጫ፥ በዛጎል ውስጥ የሚገኝ ሽቱ፥ የሚሸትትም ሙጫ፥ ጥሩም እጣን ውሰድ፤ የሁሉም መጠን ትክክል ይሁን።

35፤ በቀማሚ ብልሃት እንደ ተሠራ፥ በጨው የተቀመመ ንጹሕና ቅዱስ ዕጣን አድርገው።

36፤ ከእርሱም ጥቂት ትወቅጣለህ፥ ታልመውማለህ፤ ከዚያም ወስደህ አንተን በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ በምስክሩ ፊት ታኖረዋለህ። እርሱም የቅዱሳን ቅዱስ ይሁንላችሁ።

37፤ እንደ እርሱ የተሠራ ዕጣን ለእናንተ አታድርጉ፤ በእናንተ ዘንድም ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ይሁን።

38፤ ሊያሸትተውም እንደ እርሱ የሚያደርግ ሰው ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ።