ምዕራፍ 29።

1፤ እኔንም በክህነት እንዲያገለግሉኝ ትቀድሳቸው ዘንድ የምታደርግባቸው ነገር ይህ ነው፤ ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና ሁለት አውራ በጎች ትወስዳለህ።

2፤ ቂጣ እንጀራ፥ በዘይትም የተለወሰ የቂጣ እንጐቻ፥ በዘይትም የተቀባ ስስ ቂጣ ከመልካም ስንዴ ታደርጋለህ።

3፤ በአንድ ሌማትም ታደርጋቸዋለህ፤ ከወይፈኑና ከሁለቱ አውራ በጎች ጋር በሌማቱ ታቀርባቸዋለህ።

4፤ አሮንና ልጆቹንም ወደ መገናኛው ድንኳን ታቀርባቸዋለህ፥ በውኃም ታጥባቸዋለህ።

5፤ ልብሶችን ወስደህ ለአሮን ሸሚዝና የኤፉድ ቀሚስ ኤፉድም የደረት ኪስም ታለብሰዋለህ፥ በብልሃትም በተጠለፈ ቋድ ታስታጥቀዋለህ፤

6፤ መጠምጠሚያውንም በራሱ ላይ ታደርጋለህ፥ የተቀደሰውንም አክሊል በመጠምጠሚያው ላይ ታኖራለህ።

7፤ የቅብዓትንም ዘይት ወስደህ በራሱ ላይ ታፈስሰዋለህ፥ ትቀባውማለህ።

8፤ ልጆቹንም ታቀርባቸዋለህ፥ ሸሚዞቹንም ታለብሳቸዋለህ።

9፤ አሮንንና ልጆቹንም በመታጠቂያ ታስታጥቃቸዋለህ፥ ቆብንም ታለብሳቸዋለህ፤ ለዘላለም ሥርዓትም ክህነት ይሆንላቸዋል፤ እንዲሁም አሮንንና ልጆቹን ትክናቸዋለህ።

10፤ ወይፈኑንም ወደ መገናኛው ድንኳን በር ፊት ታቀርበዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በወይፈኑ ራስ ላይ ይጭናሉ።

11፤ ወይፈኑንም በመገናኛው ድንኳን በር አጠገብ በእግዚአብሔር ፊት ታርደዋለህ።

12፤ ከወይፈኑም ደም ወስደህ በመሠዊያው ቀንዶች ላይ በጣትህ ትረጨዋለህ፤ ደሙንም ሁሉ ከመሠዊያው በታች ታፈስሰዋለህ።

13፤ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ ሁሉ በጉልበቱም ላይ ያለውን መረብ ሁለቱንም ኵላሊቶች በላያቸውም ያለውን ስብ ወስደህ በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ።

14፤ የወይፈኑን ሥጋ ግን፥ ቁርበቱንም፥ ፈርሱንም ከሰፈር ውጭ በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የኃጢአት መሥዋዕት ነው።

15፤ አንደኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም በአውራው በግ ራስ ላይ እጆቻቸውን ይጭናሉ።

16፤ አውራውንም በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ወስደህ በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ።

17፤ አውራውንም በግ በየብልቱ ትቈርጠዋለህ፥ የሆድ ዕቃውንና እግሮቹንም ታጥባለህ፥ ከብልቱና ከራሱም ጋር ታኖረዋለህ።

18፤ አውራውንም በግ በሞላው በመሠዊያው ላይ ታቃጥላለህ፤ ለእግዚአብሔር የሚቃጠል መሥዋዕት ነው፤ ጣፋጭ ሽቱ ነው። ለእግዚአብሔር የቀረበ የእሳት ቍርባን ነው።

19፤ ሁለተኛውንም አውራ በግ ትወስደዋለህ፤ አሮንና ልጆቹም እጆቻቸውን በአውራው በግ ራስ ላይ ይጭናሉ።

20፤ አውራውንም በግ ታርደዋለህ፥ ደሙንም ትወስዳለህ፥ የአሮንንም የቀኝ ጆሮ ጫፍ፥ የልጆቹንም የቀኝ ጆሮአቸውን ጫፍ፥ የቀኝ እጃቸውንና የቀኝ እግራቸውን አውራ ጣት ታስነካለህ፤ ደሙንም በመሠዊያው ላይ በዙሪያው ትረጨዋለህ።

21፤ በመሠዊያውም ላይ ካለው ደም ከቅብዓት ዘይትም ወስደህ በአሮንና በልብሱ ላይ፥ ከእርሱም ጋር ባሉት በልጆቹና በልብሶቻቸው ላይ ትረጨዋለህ፤ እርሱም ልብሶቹም፥ ከእርሱም ጋር ልጆቹ ልብሶቻቸውም ይቀደሳሉ።

22፤ ደግሞም የሚካኑበት አውራ በግ ነውና የበጉን ስብ፥ ላቱንም፥ የሆድ ዕቃውንም የሚሸፍነውን ስብ፥ በጉበቱም ላይ ያለውን መረብ፥ ሁለቱንም ኵላሊቶች በላያቸውም ያለውን ስብ፥ የቀኙንም ወርች ትወስዳለህ።

23፤ አንድ እንጀራ፥ አንድም የዘይት እንጀራ፥ አንድም ስስ ቂጣ በእግዚአብሔር ፊት በሌማት ካለው ቂጣ እንጀራ ትወስዳለህ፤

24፤ ሁሉንም በአሮን እጆችና በልጆቹ እጆች ታኖረዋለህ፤ ለሚወዘወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትወዘውዘዋለህ።

25፤ ከእጃቸውም ትቀበለዋለህ፥ በመሠዊያውም ላይ ከሚቃጠል መሥዋዕት ጋር በእግዚአብሔር ፊት ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን ታቃጥለዋለህ፤ እርሱ ለእግዚአብሔር የእሳት ቍርባን ነው።

26፤ ለአሮንም ክህነት የታረደውን በግ ፍርምባ ወስደህ ለሚወዘወዝ ቍርባን በእግዚአብሔር ፊት ትወዘውዘዋለህ፤ እርሱም የአንተ ወግ ይሆናል።

27፤ ከሚካኑበትም አውራ በግ የተወሰደ ለአሮንና ለልጆቹ ወግ የሚሆን ለመሥዋዕት የተወዘወዘውን ፍርምባና የተነሣውን ወርች ትቀድሳለህ።

28፤ ያውም የማንሣት ቍርባን ነውና ከእስራኤል ልጆች ዘንድ ለዘላለም የአሮንና የልጆቹ ወግ ይሁን፤ የእስራኤል ልጆች የሚያቀርቡት የደኅንነት መሥዋዕታቸው የማንሣት ቍርባን ይሆናል፤ ለእግዚአብሔር የማንሣት ቍርባን ይሆናል።

29፤ የተቀደሰውም የአሮን ልብስ ይቀቡበትና ይካኑበት ዘንድ ከእርሱ በኋላ ለልጆቹ ይሁን።

30፤ ከልጆቹም በእርሱ ፋንታ ካህን የሚሆነው በመቅደስ ለማገልገል ወደ መገናኛው ድንኳን ሲገባ ሰባት ቀን ይልበሰው።

31፤ የሚካንበትንም አውራ በግ ወስደህ ሥጋውን በተቀደሰ ስፍራ ትቀቅለዋለህ።

32፤ አሮንና ልጆቹም የአውራውን በግ ሥጋ በሌማትም ያለውን እንጀራ በመገናኛው ድንኳን በር ይበሉታል።

33፤ የተካኑና የተቀደሱ ይሆኑ ዘንድ ማስተስረያ የሆነውን ነገር ይብሉት፤ ሌላ ሰው ግን አይብላው፤ የተቀደሰ ነውና።

34፤ የተካኑበትም ሥጋ ወይም እንጀራ ተርፎ ቢያድር፥ የቀረውን በእሳት ታቃጥለዋለህ፤ የተቀደሰ ነውና አይበላም።

35፤ እንዳዘዝሁህም ሁሉ በአሮንና በልጆቹ እንዲህ አድርግ፤ ሰባት ቀን ትክናቸዋለህ።

36፤ ዕለት ዕለትም ስለ ማስተስረይ ለኃጢአት መሥዋዕት ወይፈኑን ታቀርባለህ፤ ማስተስረያም ባደረግህ ጊዜ መሠዊያውን ታነጻዋለህ፤ ቅዱስም ይሆን ዘንድ ትቀባዋለህ።

37፤ ሰባት ቀን ለመሠዊያው ማስተስረያ ታደርጋለህ፥ ትቀድሰውማለህ፤ መሠዊያውም ቅድስተ ቅዱሳን ይሆናል፤ መሠዊያውንም የሚነካ ሁሉ ቅዱስ ይሆናል።

38፤ በመሠዊያውም ላይ የምታቀርበው ይህ ነው፤ በቀን በቀን ዘወትር ሁለት የዓመት ጠቦቶች ታቀርባለህ።

39፤ አንዱን ጠቦት በማለዳ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ፤ ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ቍርባን አድርገህ ታቀርበዋለህ።

40፤ ከአንዱ ጠቦትም ጋር የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ በሆነ ተወቅጦ በተጠለለ ዘይት የተለወሰ የኢፍ መስፈሪያ አሥረኛ እጅ መልካም ዱቄት፥ ደግሞ ለመጠጥ ቍርባን የኢን መስፈሪያ አራተኛ እጅ የወይን ጠጅ ታቀርባለህ።

41፤ ሁለተኛውንም ጠቦት በማታ ታቀርበዋለህ፥ እንደ ማለዳውም የእህልና የመጠጥ ቍርባን ታደርግበታለህ፤ ለእግዚአብሔር ጣፋጭ ሽቱ እንዲሆን የእሳት ቍርባን ይሆናል።

42፤ ለአንተ እናገር ዘንድ ከእናንተ ጋር በምገናኝበት በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ፥ በእግዚአብሔር ፊት ይህ ዘወትር ለልጅ ልጃችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆናል።

43፤ ከእስራኤልም ልጆች ጋር በዚያ እገናኛለሁ፤ ድንኳኑም በክብሬ ይቀደሳል።

44፤ የመገናኛውንም ድንኳን መሠዊያውንም እቀድሳለሁ፤ በክህነትም ያገለግሉኝ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን እቀድሳለሁ።

45፤ በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፥ አምላክም እሆናቸዋለሁ።

46፤ በመካከላቸውም እኖር ዘንድ ከግብፅ ምድር ያወጣኋቸው አምላካቸው እግዚአብሔር እኔ እንደ ሆንሁ ያውቃሉ፤ እኔ አምላካቸው እግዚአብሔር ነኝ።