ምዕራፍ 6።

1፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። በጸናች እጅ ይለቅቃችኋልና፥ በጸናችም እጅ ከምድሩ አስወጥቶ ይሰድዳቸዋልና አሁን በፈርዖን የማደርገውን ታያለህ።

2፤ እግዚአብሔርም ሙሴን ተናገረው አለውም። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤

3፤ ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ፤ ነገር ግን ስሜ እግዚአብሔር አልታወቀላቸውም ነበር።

4፤ የተሰደዱባትንም ምድር፥ የእንግድነታቸውን የከነዓንን ምድር፥ እሰጣቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳኔን አቆምሁ።

5፤ ደግሞ እኔ ግብፃውያን የገዙአቸውን የእስራኤልን ልጆች ልቅሶ ሰማሁ፤ ቃል ኪዳኔንም አሰብሁ።

6፤ ስለዚህም ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፥ ከግብፃውያንም ባርነት አወጣችኋለሁ፥ ከተገዥነታቸውም አድናችኋለሁ፤ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ፥

7፤ ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ፥ አምላክም እሆናችኋለሁ፤ እኔም ከግብፃውያን ባርነት ያወጣኋችሁ እግዚአብሔር አምላካችሁ እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

8፤ ለአብርሃምና ለይስሐቅ ለያዕቆብም እሰጣት ዘንድ ወደ ማልሁባት ምድር አገባችኋለሁ፤ እርስዋንም ርስት አድርጌ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

9፤ ሙሴም ይህን ለእስራኤል ልጆች ተናገረ፤ እነርሱ ግን ከሰውነታቸው መጨነቅ ከከባዱም ሥራ የተነሣ ቃሉን አልሰሙትም።

10፤ እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው።

11፤ ግባ፥ የእስራኤልንም ልጆች ከአገሩ ይለቅቅ ዘንድ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር።

12፤ ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት። እነሆ የእስራኤል ልጆች አልሰሙኝም፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? ይልቁንም እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ ብሎ ተናገረ።

13፤ እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን ተናገራቸው፥ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖንም የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ እንዲያወጣቸው ይነግሩት ዘንድ አዘዛቸው።

14፤ የአባታቸውም ቤት አለቆች እነዚህ ናቸው። የእስራኤል የበኵር ልጅ የሮቤል ልጆች፤ ሄኖኅ፥ ፈሉስ፥ አስሮን፥ ከርሚ፤ እነዚህ የሮቤል ወገኖች ናቸው።

15፤ የስምዖንም ልጆች፤ ይሙኤል፥ ያሚን፥ ኦሃድ፥ ያኪን፥ ዶሐር፥ የከነዓናዊቱም ልጅ ሳኡል፤ እነዚህ የስምዖን ወገኖች ናቸው።

16፤ እነዚህም እንደ ወገኖቻቸው የሌዊ ልጆች ስሞች ጌድሶን፥ ቀዓት፥ ሜራሪ ናቸው። የሌዊም የሕይወት ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው።

17፤ የጌድሶንም ልጆች እንደ ወገኖቻቸው ሎቤኒ፥ ሰሜኢ ናቸው።

18፤ የቀዓትም ልጆች እንበረም፥ ይስዓር፥ ኬብሮን፥ ዑዝኤል ናቸው፤ የቀዓትም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነው።

19፤ የሜራሪ ልጆች ሞሖሊ፥ ሙሲ ናቸው። እነዚህ እንደ ትውልዳቸው የሌዊ ወገኖች ናቸው።

20፤ እንበረምም የአጎቱን ልጅ ዮካብድን አገባ፥ አሮንና ሙሴንም ወለደችለት፤ የእንበረምም የሕይወቱ ዘመን መቶ ሠላሳ ሰባት ዓመት ነው።

21፤ የይስዓር ልጆች ቆሬ፥ ናፌግ፥ ዝክሪ ናቸው።

22፤ የዑዝኤል ልጆች ሚሳኤል፥ ኤልዳፋን፥ ሥትሪ ናቸው።

23፤ አሮንም የአሚናዳብን የነአሶንን እኅት ኤልሳቤጥን አገባ፥ እርስዋም ናዳብንና አብዮድን አልዓዛርንና ኢታምርን ወለደችለት።

24፤ የቆሬ ልጆች አሴር፥ ሕልቃና፥ አብያሳፍ ናቸው፤ እነዚህ የቆሬ ልጆች ወገኖች ናቸው።

25፤ የአሮንም ልጅ አልዓዛር ከፉትኤል ልጆች ሚስት አገባ፥ እርስዋም ፊንሐስን ወለደችለት። እነዚህ እንደ ወገኖቻቸው የሌዋውያን አባቶች አለቆች ናቸው።

26፤ እነዚህ አሮንና ሙሴ እግዚአብሔር። ከግብፅ ምድር በየሠራዊቶቻቸው የእስራኤልን ልጆች አውጡ ያላቸው ናቸው።

27፤ እነዚህ የእስራኤልን ልጆች ከግብፅ ያወጡ ዘንድ ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን ጋር የተነጋገሩ ናቸው፤ እነዚህ ሙሴና አሮን ናቸው።

28፤ እግዚአብሔርም በግብፅ አገር ሙሴን በተናገረው ቀን እንዲህ ሆነ፤

29፤ እግዚአብሔር ሙሴን። እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ እኔ የምነግርህን ሁሉ ለግብፅ ንጉሥ ለፈርዖን ንገር ብሎ ተናገረው።

30፤ ሙሴም በእግዚአብሔር ፊት። እነሆ እኔ ከንፈረ ቈላፍ ነኝ፤ እንዴትስ ፈርዖን ይሰማኛል? አለ።