ምዕራፍ 5።

1፤ በሦስተኛውም ቀን አስቴር ልብሰ መንግሥትዋን ለብሳ በንጉሡ ቤት ትይዩ በንጉሡ ቤት በውስጠኛው ወለል ቆመች፤ ንጉሡም በቤቱ መግቢያ ትይዩ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በንጉሡ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ነበር።

2፤ ንጉሡም ንግሥቲቱ አስቴር በወለሉ ላይ ቆማ ባየ ጊዜ በዓይኑ ሞገስ አገኘች፤ ንጉሡም በእጁ የነበረውን የወርቁን ዘንግ ለአስቴር ዘረጋላት፤ አስቴርም ቀርባ የዘንጉን ጫፍ ነካች።

3፤ ንጉሡም። ንግሥት አስቴር ሆይ፥ የምትለምኚኝ ምንድር ነው? የምትሺውስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኵሌታ እንኳ ቢሆን ይሰጥሻል አላት።

4፤ አስቴርም። ለንጉሡ መልካም ሆኖ ቢታይ ንጉሡ ወዳዘጋጀሁለት ግብዣ ከሐማ ጋር ዛሬ ይምጣ አለች።

5፤ ንጉሡም። አስቴር እንዳለች ይደረግ ዘንድ ሐማን አስቸኵሉት አለ። ንጉሡና ሐማ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ መጡ።

6፤ ንጉሡም በወይኑ ጠጅ ግብዣ ሳለ አስቴርን። የምትሺው ምንድር ነው? ይሰጥሻል፤ ልመናሽስ ምንድር ነው? እስከ መንግሥቴ እኵሌታ እንኳ ቢሆን ይደረግልሻል አላት።

7፤ አስቴርም መልሳ። ልመናዬና የምሻው ነገር ይህ ነው፤

8፤ በንጉሡ ዘንድ ሞገስ አግኝቼ እንደ ሆነ፥ ልመናዬንም ይፈጽም ዘንድና የምሻውን ያደርግ ዘንድ ንጉሡ ደስ ቢያሰኘው፥ ንጉሡና ሐማ ወደማዘጋጅላቸው ግብዣ ይምጡ፤ እንደ ንጉሡም ነገር ነገ አደርጋለሁ አለች።

9፤ በዚያም ቀን ሐማ ደስ ብሎት በልቡም ተደስቶ ወጣ፤ ነገር ግን መርዶክዮስ በንጉሡ በር ያለ መነሣትና ያለ መናወጥ ተቀምጦ ባየ ጊዜ ሐማ በመርዶክዮስ ላይ እጅግ ተቈጣ።

10፤ ሐማ ግን ታግሦ ወደ ቤቱ ሄደ፤ ልኮም ወዳጆቹንና ሚስቱን ዞሳራን አስጠራ።

11፤ ሐማም የሀብቱን ክብርና የልጆቹን ብዛት፥ ንጉሡም ያከበረበትን ክብር ሁሉ፥ በንጉሡም አዛውንትና ባሪያዎች ላይ ከፍ ከፍ እንዳደረገው አጫወታቸው።

12፤ ሐማም። ንግሥቲቱ አስቴር ወዳዘጋጀችው ግብዣ ከእኔ በቀር ከንጉሡ ጋር ማንንም አልጠራችም፤ ደግሞ ነገ ከንጉሡ ጋር ወደ እርስዋ ተጠርቻለሁ።

13፤ ነገር ግን አይሁዳዊው መርዶክዮስ በንጉሡ በር ተቀምጦ ካየሁ ይህ ሁሉ ለእኔ ምንምን አይጠቅምም አለ።

14፤ ሚስቱም ዞሳራና ወዳጆቹ ሁሉ። ቁመቱ አምሳ ክንድ የሆነ ግንድ ይደረግ፥ ነገም መርዶክዮስ ይሰቀልበት ዘንድ ለንጉሡ ተናገር፤ ደስም ብሎህ ከንጉሡ ጋር ወደ ግብዣው ግባ አሉት። ነገራቸውም ሐማን ደስ አሰኘው፥ ግንዱንም አስደረገ።