ምዕራፍ 31።

1፤ ሙሴም ሄዶ ይህንን ቃል ለእስራኤል ሁሉ ነገረ።

2፤ አላቸውም። እኔ ዛሬ መቶ ሀያ ዓመት ሆኖኛል፤ ከዚህ በኋላ እወጣና እገባ ዘንድ አልችልም፤ እግዚአብሔርም። ይህን ዮርዳኖስን አትሻገርም ብሎኛል።

3፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ በፊትህ ያልፋል፤ እርሱ እነዚህን አሕዛብ ከፊትህ ያጠፋቸዋል ትወርሳቸውማለህ፤ እግዚአብሔርም እንደ ተናገረ ኢያሱ በፊትህ ይሻገራል።

4፤ እግዚአብሔርም ባጠፋቸው በአሞራውያን ነገሥታት በሴዎንና በዐግ በምድራቸውም እንዳደረገ ያደርግባቸዋል።

5፤ እግዚአብሔርም በፊታችሁ አሳልፎ ይጥላቸዋል፥ እንዳዘዝኋችሁም ትእዛዝ ሁሉ ታደርጉባቸዋላችሁ።

6፤ ጽኑ፥ አይዞአችሁ፥ አትፍሩ፥ ከፊታቸውም አትደንግጡ፤ አምላክህ እግዚአብሔር እርሱ ከአንተ ጋር ይሄዳል፤ አይጥልህም፥ አይተውህም።

7፤ ሙሴም ኢያሱን ጠርቶ በእስራኤል ሁሉ ፊት። አንተ ከዚህ ሕዝብ ጋር እግዚአብሔር ለአባቶቻቸው እንዲሰጥ ወደ ማለላቸው ምድር ትገባለህና፥ እርስዋንም ለእነርሱ ታወርሳለህና ጽና፥ አይዞህ።

8፤ በፊትህም የሚሄድ እርሱ እግዚአብሔር ነው፤ ከአንተ ጋር ይሆናል፥ አይጥልህም፥ አይተውህም፤ አትፍራ፥ አትደንግጥ አለው።

9፤ ሙሴም ይህችን ሕግ ጻፈ፥ የእግዚአብሔርንም የቃል ኪዳኑን ታቦት ይሸከሙ ለነበሩት ለሌዊ ልጆች ለካህናቱ ለእስራኤልም ሽማግሌዎች ሁሉ ሰጣት።

10፤ ሙሴም እንዲህ ብሎ አዘዛቸው። በሰባተኛው ዓመት መጨረሻ፥ በዕዳ ምሕረት ዘመን፥ በዳስ በዓል፥

11፤ እስራኤል ሁሉ በአምላክህ በእግዚአብሔር ፊት ይታይ ዘንድ እርሱ በመረጠው ስፍራ ሲከማች፥ ይህን ሕግ በእስራኤል ሁሉ ፊት በጆሮው አንብበው።

12፤ ይሰሙና ይማሩ ዘንድ፥ አምላካችሁንም እግዚአብሔርን ይፈሩ ዘንድ፥ የዚህንም ሕግ ቃሎች ሁሉ ጠብቀው ያደርጉ ዘንድ ሕዝቡን ወንዶችንና ሴቶችን ሕፃናቶችንም በአገራችሁ ደጅ ያለውንም መጻተኛ ሰብስብ።

13፤ የሕግ ቃላት የማያውቁ ልጆቻቸውም ዮርዳኖስን ተሻግራችሁ ልትወርሱአት በምትሄዱባት ምድር በምትኖሩበት ዘመን ሁሉ ይስሙ፥ አምላካችሁን እግዚአብሔርንም መፍራት ይማሩ።

14፤ እግዚአብሔርም ሙሴን። የምትሞትበት ቀን፥ እነሆ፥ ቀረበ፤ ኢያሱን ጠርተህ እርሱን አዝዘው ዘንድ በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ከእርሱ ጋር ቁም አለው። ሙሴና ኢያሱም ሄደው በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ቆሙ።

15፤ እግዚአብሔርም በድንኳኑ ውስጥ በደመና ዓምድ ተገለጠ፤ የደመናውም ዓምድ በድንኳኑ ደጃፍ ላይ ቆመ።

16፤ እግዚአብሔርም ሙሴን አለው። እነሆ፥ ከአባቶችህ ጋር ትተኛለህ፤ ይህም ሕዝብ ይነሣል፥ ይቀመጥባትም ዘንድ በሚሄድባት ምድር መካከል ያሉትን ሌሎችን አማልክት ተከትሎ ያመነዝራል፥ እኔንም ይተወኛል፥ ከእነርሱም ጋር ያደረግሁትን ቃል ኪዳን ያፈርሳሉ።

17፤ በዚያም ቀን ቍጣዬ ይነድድባቸዋል፥ እተዋቸውማለሁ፥ ፊቴንም እሰውርባቸዋለሁ፥ ለአሕዛብ መብል ይሆናሉ፤ በዚያም ቀን። በእውነት እግዚአብሔር በእኛ መካከል የለምና ይህ ክፉ ነገር ሁሉ አገኘን እስኪሉ ድረስ ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት ይደርስባቸዋል።

18፤ ሌሎችን አማልክት ተከትለዋልና ስላደረጉት ክፋት ሁሉ እኔ በዚያ ቀን ፈጽሜ ፊቴን እሰውራለሁ።

19፤ አሁንም ይህችን መዝሙር ለእናንተ ጻፉ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተምሩአቸው፤ ይህችም መዝሙር በእስራኤል ላይ ምስክር ትሆንልኝ ዘንድ በአፋቸው አድርጓት።

20፤ ለአባቶቻቸው ወደ ማልሁላቸው፥ ወተትና ማር ወደ ምታፈስሰው ምድር ካገባኋቸው በኋላ፥ ከበሉም ከጠገቡም ከደነደኑም በኋላ፥ ሌሎችን አማልክት ተከትለው ያመልካሉ፥ እኔንም ይንቃሉ፥ ቃል ኪዳኔንም ያፈርሳሉ።

21፤ ዛሬ ወደ ማልሁላቸው ምድር ገና ሳላገባቸው የሚያስቡትን አሳብ አውቃለሁና፥ ከልጆቻቸውም አፍ አትረሳምና ብዙ ክፉ ነገርና ጭንቀት በደረሰባቸው ጊዜ ይህች መዝሙር ምስክር ሆና በፊታቸው ትመሰክራለች።

22፤ ሙሴም በዚያ ቀን ይህችን መዝሙር ጻፈ፥ ለእስራኤልም ልጆች አስተማራት።

23፤ የነዌንም ልጅ ኢያሱን። የእስራኤልን ልጆች ወደ ማልሁላቸው ምድር ታገባለህና ጽና፥ አይዞህ፤ እኔም ከአንተ ጋር እሆናለሁ ብሎ አዘዘው።

24፤ እንዲህም ሆነ፤ ሙሴ የዚህን ሕግ ቃሎች በመጽሐፍ ከጻፈ ከፈጸመም በኋላ፥

25፤ ሙሴ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት የሚሸከሙትን ሌዋውያንን እንዲህ ብሎ አዘዘ።

26፤ ይህን የሕግ መጽሐፍ ውሰዱ፥ በዚያም በእናንተ ላይ ምስክር እንዲሆን በአምላካችሁ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት አጠገብ አኑሩት።

27፤ እኔ ዓመፃችሁንና የአንገታችሁን ድንዳኔ አውቃለሁና፤ እኔም ዛሬ ከእናንተ ጋር ገና በሕይወት ሳለሁ እናንተ በእግዚአብሔር ላይ ዐምፃችኋል፤ ይልቁንስ ከሞትሁ በኋላ እንዴት ይሆናል?

28፤ ይህን ቃል በጆሮአቸው እናገር ዘንድ፥ ሰማይንና ምድርንም አስመሰክርባቸው ዘንድ የነገዶቻችሁን ሽማግሌዎች ሁሉ አለቆቻችሁንም ሰብስቡልኝ፤

29፤ ከሞትሁ በኋላ ፈጽማችሁ እንድትረክሱ፥ ካዘዝኋችሁም መንገድ ፈቀቅ እንድትሉ አውቃለሁና። በእጃችሁም ሥራ ታስቈጡት ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ስላደረጋችሁ በኋለኛው ዘመን ክፉ ነገር ያገኛችኋል።

30፤ ሙሴም በእስራኤል ጉባኤ ሁሉ ጆሮ የዚህች መዝሙር ቃሎች እስኪፈጸሙ ድረስ ተናገረ።