ምዕራፍ 23።

1፤ ቍላው የተቀጠቀጠ ብልቱም የተቈረጠ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ።

2፤ ዲቃላ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ፤ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ።

3፤4፤ ከግብፅ በወጣችሁ ጊዜ እንጀራና ውኃ ይዘው በመንገድ ላይ አልተቀበሉአችሁምና፥ በመስጴጦምያ ካለው ከፋቱራ የቢዖርን ልጅ በለዓምን ዋጋ ሰጥተው ይረግምህ ዘንድ አምጥተውብሃልና አሞናዊና ሞዓባዊ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ እስከ አሥር ትውልድ ድረስ ለዘላለም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ።

5፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር በለዓምን ይሰማ ዘንድ አልወደደም፤ አምላክህም እግዚአብሔር ወድዶሃልና እርግማኑን በረከት አደረገልህ።

6፤ በዘመንህ ሁሉ ለዘላለም ሰላምና ልማት ለእነርሱ አትሻ።

7፤ ኤዶማዊው ወንድምህ ነውና አትጸየፈው፤ ግብፃዊውንም በአገሩ ስደተኛ ነበርህና አትጸየፈው።

8፤ ከእነርሱም በሦስተኛው ትውልድ የሚወለዱ ልጆች ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ይግቡ።

9፤ ጠላቶችህን ልትወጋ በወጣህ ጊዜ ከክፉ ነገር ሁሉ ሰውነትህን ጠብቅ።

10፤ በእናንተ መካከል ሌሊት በሚሆነው ርኵሰት የረከስ ሰው ቢኖር፥ ከሰፈር ወደ ውጭ ይውጣ፥ ወደ ሰፈርም አይግባ።

11፤ በመሸም ጊዜ በውኃ ይታጠብ፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ወደ ሰፈር ይመለስ።

12፤ ወደ ሜዳም ትወጣበት ዘንድ ከሰፈር ውጭ ቦታ ይሁንልህ።

13፤ ከመሣሪያህም ጋር መቈፈሪያ ያዝ፤ በሜዳም በተቀመጥህ ጊዜ ትምስበታለህ፥ ዞረህም ከአንተ የወጣውን በአፈር ትከድነዋለህ።

14፤ አምላክህ እግዚአብሔር ሊያድንህ ጠላቶችህንም በእጅህ አሳልፎ ሊሰጥ በሰፈርህ መካከል ይሄዳልና ስለዚህ ነውረኛ ነገር እንዳያይብህ፥ ፊቱንም ከአንተ እንዳይመልስ ሰፈርህ የተቀደስ ይሁን።

15፤ ከጌታው ኮብልሎ ወደ አንተ የመጣውን ባሪያ ለጌታው አሳልፈህ አትስጥ።

16፤ ከደጆችህ በሚመርጣት በአንዲቱ በሚወድዳት ስፍራ ከአንተ ጋር በመካከልህ ይቀመጥ፥ አንተም አታስጨንቀው።

17፤ ከእስራኤል ሴቶች ልጆች ሴት ጋለሞታ አትገኝ፥ ከእስራኤልም ወንዶች ልጆች ወንድ ጋለሞታ አይገኝ።

18፤ ስለ ተሳልኸው ስእለት ሁሉ የጋለሞታይቱን ዋጋና የውሻውን ዋጋ ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ቤት አታቅርብ፤ ሁለቱም በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የሚያጸይፉ ናቸውና።

19፤ ለወንድምህ በወለድ አታበድር፤ የብር ወይም የእህል ወይም የማናቸውንም ነገር ሁሉ ወለድ አትውሰድ።

20፤ ለእንግዳው በወለድ አበድረው፤ ነገር ግን አምላክህ እግዚአብሔር ልትወርሳት በምትገባባት ምድር በሥራህ ሁሉ ይባርክህ ዘንድ ለወንድምህ በወለድ አታበድር።

21፤ ለአምላክህ ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ አምላክህ እግዚአብሔር ከአንተ ፈጽሞ ይሻዋልና፥ ኃጢአትም ይሆንብሃልና መክፈሉን አታዘገይ።

22፤ ባትሳል ግን ኃጢአት የለብህም።

23፤ በአፍህ የተናገርኸውን ለአምላክህ ለእግዚአብሔር በፈቃድህ ተስለሃልና ከከንፈርህ የወጣውን ታደርግ ዘንድ ጠብቅ።

24፤ ወደ ባልንጀራህ ወይን ቦታ በገባህ ጊዜ እስክትጠግብ ድረስ ከወይኑ ብላ፤ ወደ ዕቃህ ግን ከእርሱ ምንም አታግባ።

25፤ ወደ ባልንጀራህ እርሻ በገባህ ጊዜ እሸቱን በእጅህ ቀጥፈህ ብላ፤ ወዳልታጨደው ወደ ባልንጀራህ እህል ግን ማጭድ አታግባ።