ምዕራፍ 22።

1፤ የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ብታይ ቸል አትበል፤ ወደ ወንድምህ መልሰው።

2፤ ወንድምህም በአቅራቢያህ ባይሆን ወይም ባታውቀው ይዘህ ወደ ቤትህ ትገባለህ፤ ወንድምህ እስኪሻው ድረስ በአንተ ዘንድ ይቀመጣል፥ ለእርሱም ትመልሰዋለህ።

3፤ እንዲህም በአህያው ወይም በልብሱ ታደርጋለህ፤ እንዲህም በወንድምህ በጠፋበት ነገር ሁሉ ባገኘኸው ጊዜ ታደርጋለህ፤ ቸል ልትለው አይገባህም።

4፤ የወንድምህ አህያ ወይም በሬው በመንገድ ወድቆ ብታይ ከእርሱ ጋር ሆነህ አነሣሣው እንጂ ቸል አትበለው።

5፤ ሴት የወንድ ልብስ አትልበስ፥ ወንድም የሴት ልብስ አይልበስ፤ ይህን የሚያደርግ በአምላክህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነውና።

6፤ በመንገድ ስትሄድ በዛፍ ወይም በመሬት ላይ እናቲቱ በጫጩቶችዋ ወይም በእንቍላሎችዋ ላይ ተኝታ ሳለች የወፍ ጎጆ ብታገኝ፥ እናቲቱን ከጫጩቶዋ ጋር አትውሰድ።

7፤ ነገር ግን መልካም ይሆንልህ ዘንድ ዕድሜህም ይረዝም ዘንድ እናቲቱን ስደድ፥ ጫጩቶችንም ለአንተ ውሰድ።

8፤ አዲስ ቤት በሠራህ ጊዜ ማንም ከእርሱ ወድቆ ደሙን በቤትህ ላይ እንዳታመጣ በጣራው ዙሪያ መከታ አድርግለት።

9፤ የዘራኸው ዘርና ከወይኑ የወጣው አንድ ሆነው እንዳይጠፉብህ በወይንህ ቦታ ላይ ሁለት ዓይነት ዘር አትዝራ።

10፤ በበሬና በአህያ በአንድነት አትረስ።

11፤ ከተልባ እግርና ከበግ ጠጕር በአንድነት የተሠራ ልብስ አትልበስ።

12፤ በምትለብሰው በልብስህ በአራቱ ማዕዘን ዘርፍ አድርግ።

13፤ ማናቸውም ሰው ሚስት ቢያገባ፥ ከደረሰባትም በኋላ ቢጠላት፥

14፤ የነውር ነገር አውርቶ። እኔ ይህችን ሴት ሚስት አድርጌ አገባኋት፥ በደርስሁባትም ጊዜ ድንግልናዋን አላገኘሁባትም ብሎ በክፉ ስም ቢያሳጣት፥

15፤ የብላቴናይቱ አባትና እናት የድንግልናዋን ምልክት ወስደው በበሩ በአደባባይ ወደ ተቀመጡ ወደ ከተማ ሽማግሌዎች ያምጡት፤

16፤ የብላቴናይቱም አባት ሽምግሌዎቹን። እኔ ለዚህ ሰው ልጄን ዳርሁለት እርሱም ጠላት፤

17፤ እነሆም። በልጅህ ድንግልና አላገኘሁባትም ብሎ የነውር ነገር አወራባት፤ የልጄም ምልክት ይኸው ይላቸዋል። በከተማም ሽማግሌዎች ፊት ልብሱን ይዘረጋሉ።

18፤ የዚያችም ከተማ ሽማግሌዎች ያንን ሰው ወስደው ይግረፉት፤

19፤ በእስራኤል ድንግል ላይ ክፉ ስም አምጥቶአልና መቶ የብር ሰቅል ያስከፍሉት፥ ለብላቴናይቱም አባት ይስጡት፤ እርስዋም ሚስት ትሁነው፥ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም።

20፤ ነገሩ ግን እውነት ቢሆን፥ በብላቴናይቱም ድንግልናዋ ባይገኝ፥

21፤ ብላቴናይቱን ወደ አባትዋ ቤት ደጅ ያውጡአት፥ በእስራኤልም ዘንድ የማይገባውን ነገር አድርጋለችና፥ በአባትዋም ቤት አመንዝራለችና የከተማዋ ሰዎች እስክትሞት ድረስ በድንጋይ ይውገሩአት፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ።

22፤ ማናቸውም ሰው ከሌላ ሰው ሚስት ጋር ተኝቶ ቢገኝ፥ አመንዝራውና አመንዝራይቱ ሁለታቸው ይሙቱ፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከእስራኤል ታስወግዳለህ።

23፤ ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ልጃገረድ ቢያጭ፥ ሌላ ሰውም በከተማ ውስጥ አግኝቶ ከእርስዋ ጋር ቢተኛ፥

24፤ ሁለቱን ወደዚያች ከተማ በር አውጡአቸው፤ ብላቴናይቱ በከተማ ውስጥ ሳለች አልጮኸችምና፥ ሰውዮውም የባልንጀራውን ሚስት አስነውሮአልና እስኪሞቱ ድረስ በድንጋይ ውገሩአቸው፤ እንዲሁም ክፉውን ነገር ከመካከልህ ታስወግዳለህ።

25፤ ነገር ግን ሰው የታጨችውን ልጃገረድ በሜዳ ቢያገኛት፥ በግድ አሸንፎም ቢደርስባት፥ ያ የደረሰባት ሰው ብቻውን ይገደል።

26፤ በብላቴናይቱ ላይ ግን ምንም አታድርጉ በብላቴናይቱ ላይ ለሞት የሚያበቃ ኃጢአት የለባትም፤ ሰው በባልንጀራው ላይ ተነሥቶ እንደሚገድለው ይህ፤ ነገር ደግሞ እንደዚሁ ነውና፤

27፤ በሜዳ ባገኛት ጊዜ የታጨችው ልጃገረድ ጮኻለችና፥ የሚታደጋትም አልነበረምና።

28፤ ማናቸውም ሰው ድንግልና ያላትን ያልታጨች ልጃገረድ ቢያገኝ፥ ወስዶም ቢደርስባት፥ ቢያገኙትም፥

29፤ ያ የደረሰባት ሰው አምሳ የብር ሰቅል ለብላቴናይቱ አባት ይስጥ፤ አስነውሮአታልና ሚስት ትሁነው፤ በዕድሜውም ዘመን ሁሉ ሊፈታት አይገባውም።

30፤ ማናቸውም ሰው የአባቱን ሚስት አይውሰድ፥ የአባቱንም ልብስ ጫፍ አይግለጥ።